መሣፍንት ባዘዘው: ጎንደሬ አድምጥ!

ጎንደሬ አድምጥ!
(መሣፍንት ባዘዘው)ዛሬ ልወርድብህ ነው! ከዛ መሃል ፒያሳ ላይ ከቆመው የመይሳው ሃውልት ላይ ተለጥፈህ ፎቶ መነሳትህን ተው!! ለጊዜው የቴዲ ልጅ ነኝ እያልክ መዝፈኑንም ያዝ አድርገው።ጀግና ሳንሆን የጀግና ልጅ ነኝ እያሉ መኮፈስ ይብቃን!! የቴዎዽሮስ ሃሞት እንጥፍጣፊዋ እንኳ ከኛ ዘንድ ሳትኖር እንዴት የጀገናውን ስም በከንቱ እንጠራዋለን?

ወልቃይት ሲቆረስ ዝም! ጠገዴ ሲቆረስ ዝም! ዋልድባ ሲታረስ ዝም! አርማጭሆ ሲሸጥ ዝም! የቴዎድሮስ ሃገር ቋራ ሲሸጥ ዝም! ትውልድ በጫት ሱስ እዬደነዘዘ ፣ የትምህርት ፖሊሲው ጥራት እያሽቆለቆለ… እያዬህ “እምቢ!” ማለት ካቃተህ የቴዎድሮስ ልጅ ነኝ አትበለኝ። አሁንስ በዛ ብለህ መነሳት ከቃተህ …እንኳን ከመይሣው ሃውልት ላይ ፎቶ ልትነሳ ነው እና በአጠገቡ ማለፍ የለብህም። እውነት እኔ እዛ ሃውልት ላይ ተደግፌ ፎቶ መነሳት አፍራለሁ። ሌላውን ሁሉ ተወው! እስኪ የወያኔን ሃሳብ ከመደገፍ ተቆጠብ።እስኪ መጀመሪያ በሃሳብ ደረጃ “እምቢ!” በል!

እስኪ ግራ እና ቀኝህን ተመልከት! ያቺ የተቀደሰች ከተማ በጫት ቤቶች ስትሞላ እየታዬህ አይደለም?ትንንሾችህ በአንተ እግር እዬተተኩ ወደ ሱስ እዬገቡ እንደሆን አስተውለሃል? ከ20 አመት በፊት የነበሩት ቸቸላ ሆስፒታል እና ፖሊ ክሊኒክ ስንት ሆስፒታል እና ክሊኒክ ተጨመረላቸው? ወገንህን እሲኪ ቸቸላ ላይ ሄደህ እየው…ሜዳ ላይ እንደ ምናምንቴ ወዳድቆልሃል!ፋሲለደስ ስንት ሃይድኩል ወለደ? ምንም!! ስንት ፋብሪካ ተተከለ? …… የወያኔን ሴራ ከአንተ የበለጠ ማን ያውቀዋል? እና ምነው ተኛህ? ኧረ ንቃ!!!

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እዬተቧደንክ ከመነታረክ እስኪ ስለ ቴዎድሮስ መንፈስ ተወያይ። እውነት የቴዎድሮስ ልጅ መሆናችንን በተግባር እናሳይ!! ዘፈን ብቻ ሰለቸኝ!! የኛም ትውልድ ቴዲን አምጦ ይውለድ እና መጭው ትውልድ ይዝፈንልን!! በየመጠጥ ቤቱ የአራዳ ልጅ፣ የፒያሳ ልጅ እያልክ በቢራ ጠርሙስ ስትፈነካከት ለም መሬትህ ለሱዳን ተቸብችቦ አለቀልህ…እስኪ በየቀበሌ መቧደንክን ትተህ አንድ ሁን እና በጠላትህ በወያኔ ላይ ተነስ!!

የተዋበች የምንተዋብ ፣የጥሃይቱ ሴት ልጆች በየሺሻ ቤቱ ሲውሉ እያዬህ እንዴት አስቻለህ? ከትንንሽ እህቶችህ ጋር የሺሻ ገመድ እዬተቀባበልክ ስታጨስ ምንም አይሰማህም?? ኧረ እንደተኛን ነግቶ ተመልሶ መሸ………