Demeke Kebede: አገርና ፊደል ( ከደሃ ህዝብ ችግር ይልቅ ቃል በመሰንጠቅ ለሚዳክሩ )

አገርና ፊደል
//ደመቀ ከበደ – አዲስ አበባ//( ከደሃ ህዝብ ችግር ይልቅ ቃል በመሰንጠቅ ለሚዳክሩ )ዝናብ ባጣ መሬት – ስንጥቅጥቅ ባለ – ውሃ በተጠማ
ዘር አበቅል ብሎ – ሁሌ እጁ ለሚላጥ – ሰርክ ለሚደማ
አንደዜ ለእግዜሩ
አንደዜ ለአውጋሩ
ጎንበስ ቀና ለሚል – አንገት ለሚደፋ
በሽህ ዘመን ሞፈር – አፈር ለሚገፋ
‹‹ሀ›› ማለት ምንድን ነው?
‹‹ለ›› ማለትስ ምንድን?
በፊደል ላይጠግብ – ጎኑ ላይደነድን፤ፊደልን በለየ – ፊደል በቆጠረ
ከፊደል ጋር ውሎ – ፊደል ጋር ባደረ
በፊደል ‹‹ልህቀት›› ላይ – ‹‹ዕውቀት›› ባደደረ
ምስኪን የአገር ድሃ
ሲሻ ‹‹የተማረ›› – ‹‹የተመራመረ››
ከችግሩ ጋራ – አለ እየዳከረ፤

ከ‹‹ሀ›› እና ‹‹ሁ›› በላይ
ለእኛነት ሾተላይ
‹‹ችጋር›› ሆኖ ሳለ – የህልማችን ሰማይ – የህዝባችን ስቃይ
መንጋ ‹‹እኔ ልብላ›› ባይ
መንጋ ‹‹እኔ አውቃለሁ›› ባይ
የፊደል አድርባይ
ፊደል አቀባብሎ – ፊደል ይተኩሳል – ይኸው በአደባባይ፤

በቁራጭ አጎዛ – ጥቀርሻ ጎጆው ውስጥ
ታጥፎ ለሚተኛ – ገበሬው አባቴ
ካለቀ ጫካ ውስጥ – ቅጠል በጀርባ አዝላ
ዳቦ ለምትጋግር – መከረኛ እናቴ፤
ነገን የኔ ብለው – በሰለለች ተስፋ – ለሚውተረተሩ
ከ‹‹አዋቂ ነን›› ባዮች
ከ‹‹ምሁር ነን›› ባዮች
ከነ ‹‹ፊደል ጭንቁ›› – መፍትሄ አለ ብለው – ለሚያጨነቁሩ
ለደሃ አገር ህዝቦች – ‹‹ምን ልሁን›› ለሚሉ……
ሶፋ ተደግፎ – ‹‹ላፕቶፕ›› ተንተርሶ
መለኪያ ጨብጦ – ወፍራም ፒፓ ጎርሶ
ቃል እየመተሩ – እየለዩ ጎራ
‹‹የለም ‹ሀ› ነው›› ማለት
‹‹አይ ‹ፐ› ነውንጅ›› – ማለት በየተራ
ይህ የ‹‹ቃል›› ስንጠቃ – የ‹‹ፊደል›› ድርደራ
ከቶ ምን ማለት ነው?
ካልሆነ በስተቀር – እውነቱን ስወራ!!

እንጂማ ….
ለኔ ብጤ ደሃ
‹‹ሀ›› ቢሉት ምኑ ነው? – ‹‹ለ›› ማለትስ ምንድን?
ፊደል እህል ሆኖ – ጎኑ ላይደነድን፤

ደግሜ ደግሜ – አሁንም እላለሁ
ለአንዲት ደሃ አገር ህዝብ
‹‹ሀ›› ማለት ምንድን ነው? – ስል እጠይቃለሁ፤
የምሬን እኮ ነው
‹‹ሀ›› ማለት ምንድን ነው? – ‹‹ለ›› ማለትስ ምንድን?
ፊደል እህል ሆኖ
ከችጋር ላይፈውስ – ከጠኔ ላያድን!!

%d bloggers like this: