በቋራ ያሉ የናይጄሪያ ዘላኖችና ‹ሸውሽዌ› ክፍል ፪

By Muluken Tesfaw

በቋራ ያሉ የናይጄሪያ ዘላኖችና ‹ሸውሽዌ›

ክፍል ፪

በዚህ በርሃና ጫካ ብዙ ገራሚ ነገሮች አሉ፡፡ መንደሮች በድንገት በሚነሳ ቋያ ሙሉ በሙሉ ይድማሉ፡፡ በርሜልን ጨምሮ ብዙዎቹ የሰፈራ መንደሮች በበርሃ ቋያ በየጊዜው እየወደሙ እንደገና ይሰራሉ፡፡ የበርሃ ሰው ተስፋ አይቆርጥም፤ ነገ በቋያ ቤቱ እንደሚወድምበት እያወቀ እንደገና ይገነባል፤ ይቃጠልበታል፤ ይሰራል…

በየመንገዱ ጅራታቸው የውሻ ያክል የረዘመ በጎች በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ በጎች ‹ፈላታ› በመባል ይታወቃሉ፡፡ ፈላታዎች የናይጀሪያ ዘላኖች በጎች ናቸው፡፡ በጎቹ በዘላኖቹ ስም ፈላታ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ የናይጀሪያ ዘላኖች የሱዳንና የቻድን መሬት አልፈው ለምን ቋራ እንደከተሙ ለኔ ብዙ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ነገር ግን ቋረኞች እንደሚሉት በቋራ ጫካዎች ውስጥ ፈላታዎች ከብቶቻቸውንና በጎቻቸውን ያረባሉ፡፡ እርግጥ ነው አካባቢው የግጦሽ ሳርና ውኃ ችግር ስለሌለበት ለከበት አርቢዎች ምቹ ቦታ ነው፡፡ የፈላታ ከብቶች አውሬዎች ናቸው፡፡ አበሻ ካዩ አባርረው ይዋጋሉ፡፡ ብዙ ግዜ አበሻዎች ከዛፍ ካልወጡ በስተቀር አያመልጧቸውም፡፡ ነገር ግን አበሾች የፈለታዎችን ከብቶች በጥይት በመምታት እንደሚወስዱባቸው ሰምቻለሁ፡፡ የፈላታ በጎች ተራብተው በድፍን ቋራና መተማ በብዛት አሉ፡፡ መልካቸው ነጫጭ ሲሆን ጸጉር የላቸውም፡፡ ጅራታቸው ረጅም ነው፡፡ ሥጋቸው ቆንጆ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እርግጥ ነው የሔድኩበት ቀን አርብ በመሆኑ የበግ ሥጋ አልበላሁም፡፡

ወደ ጫካ አንድ ሰው ጂፒኤስ ሳይዝ ከሔደ የመጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ የመጣ የመንግሥት ተቀጣሪ ከሆነ መስክ ብቻውን መሔድ የለበትም ይላሉ፡፡ ወደ ጫካው ከሔደ በኋላ በርሃው ሕሊናውን ያነሆልለዋል፡፡ በበርሃ ሕሊናን የመሳት ሒደት ‹ሽውሽዌ› ይባላል፡፡ ሽውሽዌ የያዘው ሰው አቅሉን ስቶ ከመጓዝ ውጭ ወደየትና እንዴት እንደሚሔድ አያውቅም፡፡ በዚህ በርካታ ሰዎች ጠፍተው ቀርተዋል አሉ፡፡ ‹አሉ› የምለው ሰዎች በነገሩኝ መሠረት ስለምነግራችሁ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህች ሽሽዌ የምትባል ‹ነገር› አንዳች መለኮታዊ ነገር ይኑራት አይኑራት የሚታወቅ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ብዙ ሰዎች እንደ ሰይጣናዊ ሥራ የሚቆጥሩት አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የአየር ንብረቱ ሞቃታማ መሆን የሰውነታችን ሥነ ሕይወታዊ (ፊዚዎሎጅካል) ሥራ ስለሚያወከው አእምሯችን በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ያቅተዋል፡፡ በዚህም አቅጣጫ የመለየት ችግር ይገጥመናል የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን የትኛው ትክክል እንደሆነ የተሰራ ጥናት አላየሁም፡፡ አቅጣጫ ሲጠፋ በአካባቢው የሚኖሩት ጉምዞች አቅጣጫን ለማወቅ የሚሆናቸው የለም፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ አሉ፡፡ አንዲት ግብርና ተመድባ የመጣች ሴት ወደ ጫካው የገጠር አካባቢ ትሔዳለች፡፡ ብዙ እንደተጓዘችም ሽውሽዌ ትይዛታለች፡፡ ያኔ ወደየት እንደምትሔድ ሳታውቅ ብዙ ከገለጎ (የወረዳው ከተማ) ርቃ ሒዳለች፡፡ በዚህም ከፈላታዎች እጅ ትገባለች፡፡ እንደነገሩኝ ከሆነ ይህች ልጅ ፈላታዎችን አግብታ እርሷም ዘላን ሆና በመኖር ላይ ነች፡፡

ፈላታዎች ሴቶችን ጠልፈው ወይም ሽውሽዌ ከወሰደላቸው መቼም አይለቁም፡፡ በዚህ የተነሳ ይህች ሴት አንዳንዴ ለዘመዶቿ ደብዳቤ ከመጻፍ የዘለለ ከጫካ ውጭ ያለውን ዓለም በሽውሽዌ ከተጠለፈችበት ጊዜ ጀምሮ አይታው አታውቅም፡፡ ለማምለጥ ብትሞክር በፈላታዎች ጥቃት ስለሚደርስባት አስባም የምታውቅ አይመስልም፡፡ ፈላታዎች ብዙም ልብስ መልበስ የለመዱ አይደሉም፡፡ በሬዎቻቸውም ሆነ እነርሱ የማሽተት ኃይላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አደጋ ከመጣባቸው አሊያም አበሻ እየቀረባቸው መሆኑን ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት አውቀው ይርቃሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አእዋፍም የሚታዘዟቸው ይመስላል፡፡ ወደ እነርሱ እየቀረበ ያለው ሰው ይሁን ሌላ አንበሳ ሁሉንም አእዋፍ ሊነግሯቸው እንደሚችል የወሬ ምንጮቼ ያረጋግጣሉ፡፡

የአካባቢውን ማኅበረሰብ ወባ፣ እባብና ሽውሸዌ ያጠቁታል፡፡ መርዛማ የበርሃ እባብ አለ፡፡ በእጽ የሚከላከሉት ሰዎችም አሉ፡፡ እርግጥ እባብ የሚከላከሉበት እጽ ከሱዳን አስማተኞች የተገኘ ነው አሉ፡፡ አዲስ አበባ እባብ ስለሌለ ጥበቡን ማወቅ እንጅ እጹን አልፈለግኩትም፡፡ ስለዚህ ይዤ አልተመለስኩም፡፡ ጥበቡንም አልቀሰምኩም፡፡ ደሞስ መሥራት አለመሥራቱን ሳላረጋግጥ እንደኔ ዓይነት ቶማስ (ተጠራጣሪ) እንዴት ይዞ ይመጣል? ሽውሽዌ ብዙ ሰው ታጠቃለች፡፡ አንድ ጊዜም እንዲሁ ከቋራ ወረዳ ወደ ገጠር የተላኩ አምስት ያክል ባለሙያዎች በሽውሽዌ ይጠቃሉ፡፡ ሕሊናቸው ነሁልሎ የሚሔዱበትን አቅጣጫ ሳቱ፡፡ ሽውሽዌ የተጠቃ ሰው ያለ አቅጣጫው ኃይሉ እስከሚያልቅ ድረስ መጓዝ ነው፡፡ የእነዚህ ባለሙያዎች ኃይል አልቆ ኖሮ ወደቁ፡፡ ወዳጆቻቸው ለመፈለግ ሞከሩ፡፡ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለሌላ መስክ (ፊልድ) የተላኩ ሰዎች በርሃ ውስጥ ወዳድቀው በክረምት ዝናብ ሣር በቅሎባቸው ተገኘ አሉ፡፡ እንግዲህ ስለ ሸውሸዌና ፈላታ ናይጀሪያውያን ካላይ ያወጋሁት በሙሉ በቋረኞች በተነገረኝ መሠረት እንጅ ከፈለታ በግ ውጭ ያየሁት አንድም ነገር የለም፡፡ እርግጥ ነው ሁሉምን ለማየት አይቻለም፡፡ ደግሞም አደገኞች ናቸው፡፡ ሽውሽዌን ልይ ብል ተመልሦ ይህን ሪፖርት ማን ያስነብባችኋል? ዘላኖቹንም ማግኘት ሌላው ከባድ ነገር ነው፤ ደግሞም የሚመጡበት ወቅት አላቸው እንጅ ዓመቱን በሙሉ አይኖሩም፡፡ እባብ እንኳን በእውን በናሽናል ጂኦግራፊ ሳየውም ውቃቢየ አይወደው፡፡ በወባ ለመለከፍ አንድ ቀን ማደር ይጠበቅብኛል፡፡ ሁሉንም ግን አልሻም፡፡ የሔድኩባት ፒክ አፕ ወደ ሸኽዲ ትመለሳች፡፡

ጊዜ ቢኖረኝ ኖሮ ብዙ ነገር የሚታይ ነበር፡፡ ወደ ደጋማው የቋራ አካባቢ ቴዎድሮስ ከተማ የሚባል አለ፡፡ እዚያ የአጼ ቴዎድሮስ የልጅ ልጆችና ዘሮች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እነርሱን የማግኘት እቅድ ነበረኝ፡፡ ጊዜም ገንዘብም ስለተመናመነ ብሎም ቀጣይ ጉዞ ስላለብኝ ያን በርሃ ትቼው መመለስ ግድ ይላል፡፡ ወጣሁም፡፡ ሸኽዲ ከተማ ባጃጅ ውስጥ ያነበብኩት ጥቅስ ለአካባቢ ምቹ (ኢንቫሮንመንት ፍሬንድሊ) ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ‹የሰው ትርፍ የለውም› የሚል ጥቅስ እዚህ ቦታ አይታሰብም፡፡ ትርፍ አትጫን የሚል ሕግ የለምና፡፡ ባጃጅ ውስጥ ያለው ጥቅስ ‹ጊዜን አይቶ የማይከዳ ዕውነተኛ ጓደኛ የበርሃ ጥላ ነው› ይላል፡፡ ከዚህ የበለጠ ዕውነት በዚህ አካባቢ የለም፡፡ ቀን ላይ አይቸዋለሁና፡፡

አሁን እየመሸ ነው፡፡ ጀምበር መዘቅዘቅ ጀምራለች፡፡ ወደ ጎንደር የሚሔዱ መኪናዎችም ብዙ የሉም፡፡ ወደፊት 161 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅብኛል፡፡ ያገኘዋት ሚኒ ባስ በዚያ ሙቀት ሰው ጥቅጥቅ አድርጋ ሞላች፡፡ ጋቢና ነበርኩ፡፡ ጋቢና ሾፌሩን ሳይጨምር ሦስተኛ ሰው ታከለልን፡፡ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ ዝም ብሎ መጓዝ ነው፡፡ ገንዳ ውኃን አለፈን፤ ደረቅ አባይ፤ ነጋዴ ባህር፤ አርሴማ፣ ሰራባ፣ ጭልጋ…. ጎንደር ምሽት ሦስት ሠዓት ሲሆን፡፡ ነገ ቀጣይ ጉዞ አለ፡፡ ወደ አርማጭሆ፡፡

በላንድ ማርክ ሆቴል የተደረገው የወልቃይት ጉዳይ ስብሰባ

የአርማጭሆን ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ግን ትናንት በጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል ስለነበረው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ስብሰባ የታዘብኩት ማስቀመጥ እሻለሁ፡፡ ሐሙስ እለት ላንድ ማርክ ሆቴል ስደርስ የእቴጌ ምንትዋብ የስብሰባ አዳራሽ ሞልቶ መፈናፈኛ አልነበረውም፡፡ ውስጥ ገብቼ አንዳንድ ነገሮችን ሪከርድ ለማድረግ ብሞክርም መሹለኪያ መንገድ ጠፋ፡፡ ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ ውጭ ላይ ሆኖ በሞንታርቦው የሚነገረውን ማዳመጥ ነበር፡፡ ስብሰባውን የአዘጋጁት የጎንደርና የዳባት አገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ወልቃይት ቀድም ባሉት ጊዜያት የቆላ ወገራ አካል ሆኖ አውራጃው ዳባት ነበር፡፡ በዚህም ይመስላል የዳባት የአገር ሽማግሌዎች ከጎንደር ከተማ ጋር በመቀናጀት ስብሰባውን የአዘጋጁት፡፡ ኮሚቴዎቹ የደረሱበትና እየገጠማቸው ያለውን ነገር ሲያስረዱ ሕዝቡ ላይ የቁጭት፣ የንዴትና የተስፋ ስሜቶች ተደባልቀው ይነበቡ ነበር፡፡ በዚሁ ሰሞን በወልቃይት፣ በጠገዴና በኹመራ አካባቢዎች ለሠፈራ ከመጡት የትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ በመኪና እየተጫኑ እየመጡ ‹‹ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለንም፤ ጸረ ሰላም ኃይሎችን አንታገስም…›› ወዘተ የሚሉ የማወናበጃና የማስፈራሪያ መፈክሮች በሰፊው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተዋቸው ሲስተናገዱ ሰንብተው ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ተወላጆች ነን ላሉት እንኳንስ ሰላማዊ ሰልፍ ሊፈቀድ ቀርቶ የቤት ውስጥ ስብሰባም ተከልክለዋል፤ አማርኛ ሙዚቃ እንዳያደምጡ ተደርገዋል፡፡ አልፎም ወደ አገራቸው ለመሔድ ኬላዎችን ተሸለክልከው ነው፡፡

የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ከሆኑት መካከል ኮሎኔል ደመቀ የሚባሉት ይህን አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹የእነርሱን ትግሬነት እኛ አልካድንም፤ እኛ የምንለው የእኛም አማራነት ይታወቅ ነው፡፡ አማራ የሆነ ሰው እንዴት በግዴታ ትግሬ ሊሆን ይችላል? በግዴታ እንዴት ማንነት ሊሰጠን ይችላል? እኛ እኮ በትግርኛ መርዶ ሰምተን በአማርኛ የምናለቅስ ነን፤ በትግርኛ የሰርግ ጥሪ ተላልፎልን በአማርኛ የምንዘፍን ሕዝብ ነን፡፡ ሕወሓት ጭቆና ወደ ጫካ አስወጣኝ ብሎ እኛ ላይ ያልፈጸመው በደል የለም፡፡ አማራ ነን ብሎ መናገር ምንድን ነው ጸረ ሰላም የሚያስብለው? ጠመንጃ መያዝ ለወልቃይት ሕዝብ ተራ በጣም ተራ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ይህ የሚጠቅም ነገር ስላልሆነ በሕገ መንግሥቱና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ጥያቄያችን እየቀርብን ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የወልቃይት ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለማውገዝ የግድ አማራ መሆን አይጠበቅም፡፡ ትግሬዎች ራሳቸው ሕወሓትን በቃህ ሊሉት ይገባል›› በማለት በሰፊው አብራሩ፡፡ አቶ አታላይ ዛፌ የተባሉም በወልቃይት ሕዝብ በተለይ ደግሞ በሱዳን ወታደሮች እየተወሰዱ ስላለቁት የአማራ ወጣቶች፣ በሕወሓት ባለሥልጣናት ስለተደፈሩት ሴቶችና ተማሪዎች፣ ግሕንብ የምድር እስር ቤት ውስጥ ስላለቁት ወልቃይቴዎች በሰፊው ሲዘረዝሩ አንዳንዶች ያለቅሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ያጨበጭቡ ነበር፡፡ ፍጹም ድብልቅልቅ ያለ ስሜት፤ በቃ ደስታና ሀዘን፣ ተስፋና ተስፋ መቁረጥ፣ የዋህነትና በቀል፣ የአንድነትና የልዩነት…. ስሜቶች በአንድ ሰው ገላ ላይ ሳይታዩ አልቀረም፡፡

አንድ ስሙን ሳልሰመው ያለፈኝ የወልቃይት ተወላጅ ሁለቱን ወንድሞቹን የሕወሓት የጸጥታ ቡድኖች ወስደው እንዴት አሰቃይተው እንደገደሉበት ምስክርነቱን ሊሰጥ ማይክራፎኑን (የድምጽ ማጉያውን) ተቀበለ፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ምንም እንኳ ግፉ የተፈጸመው ከዐሥር ዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም ድረስ በሐዘኑ ልቦናው እንደተሰበረ ነው፡፡ ሊናገር ሲል ትናገው መከፈት አልቻለም፡፡ በዐይኑ እንባ ፈሰሰ፡፡ ድምጹ ተቆራረጠ፡፡ ብዙ በጣም ብዙ በስብሰባው የነበሩ ሰዎች ዝም ብለው ማዳመጥ አልቻሉም፡፡ የሰዎች ኪስ ሲንኮሻኮሽ ይሰማል፡፡ ሶፍት ወይም ማኅረም ፍለጋ ነበር፡፡ የዛሬ ዐሥር ዓመት የተገደሉ ሰዎች ዛሬ መርዶአቸው የተረዳ መሠለኝ፡፡ ወንድ ልጅ ሲያለቅስ ማየት አልወድም፡፡ ቀረጻ ላይ ነበርኩ፡፡ እንባየ ተናነቀኝ፤ ታገልኩት፤ አልቻልኩም ፈሠሠ፡፡

ግለሰቡ ወንድሞቹን ከእናታቸው ነጥለው ወስደው አሰቃይተው ገድለውበታል፡፡ እርሱም አገር አለኝ ብሎ ተመልሶ አያውቅም፡፡ እንኳን ወልቃይት ሊሔድ ቀርቶ ጎንደር ኹመራ መውጫን ወለቃን አልፎ አያውቅም፡፡ በሐዘን የተሰበረ ልብ ይገርማል፡፡ በወልቃይት ሕዝብ ላይ ሕወሓት የፈጸመው ግፍ በቀላሉ ተነግሮ እንደማያልቅ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ሰዎች ተገድለው በአዲ ረመጥ ከተማ በመኪና ላይ ተጭነው ለሕዝብ መቀጣጫ እንዲሆኑ እንደ ደርግ የቀይ ሽብር ሰለባዎች በዚህ ዘመን የተፈጸመው ከወልቃይት ሕዝብ ውጭ የትም አይኖርም፡፡ አማራ በግዴታ ወደ ትግሬነት የተቀየረው ከወልቃይት ሕዝብ ውጭ በአገራችንም በዓለማችንም አይኖርም፡፡ እውነታው ይሔ ነው፡፡ ከሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እኛም ጋ መጥታችሁ ጉዳዩን አስረዱን የሚሉ ጥያቄዎች ብዙ ነበሩ፡፡

ጎንደር ስሔድ ምሽት ላይ ብዙ ጊዜ ወደ አጼ በካፋ የባህል ምሽት ማዝገሜን አልተውም፡፡ ጥሎብኝ የዚህ የባህል ምሽት እወደዋለሁ፡፡ የዛሬው አካሔዴ ግን ለመዝናናት እንዳልሆነ ብናገር ተአማኒነት ስለማይኖረው ብዙም ምክንያት ማቅረብ አልሻም፡፡ ብዙ ዜጎቻችን በርሃብ ጠኔ የሚበሉትን አጥተው እየተቸገሩ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህንንም አይቻለሁ፡፡ በሰፊው ወደፊት ስለምሔድበት አሁን አልቀላቅልም፡፡ ቀን ላይ በወልቃይቶች ላይ የደረሰውን ስሰማ በእውነቱ እድሜ ልኬን በሐዘን የምኖርም መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ጠንካራ ፍጥረት ነውና የሐዘን ብዛት አጥንቱን አይሰብረውም፤ የመደሰቻ ሕዋሳቱን አያደነዝዝም እንጅ ትንሽ ብቻ በቂ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ አዝማሪ ምን አለ ለማለት ነበር የገባሁት፡፡

ተንኮለኛው ጋዜጠኛ ተስፋየ ገብረ አብ አንድ ጊዜ ጎንደር ሒጄ ሰማሁት ያላቸውን የአዝማሪ ግጥሞች አስታወስኩ፡፡

ጎንደር አገር ጠፍቶ ሲፈለግ ሌሊት

ቀን ታዲሱ ጋራ ሲሔድ አየሁት፤

በረከት አገሩ ስለናፈቀው

ዳሸን አናት ሆኖ አስመራን አየሁ፡፡

እነዚህን ግጥሞች ጎንደር በሔድኩ ቁጥር አዝማሪ ለአዝማሪ ቤት እየዞርኩ ልሰማቸው ፈልጌ አልተሳካልኝም፡፡ ግን የጎንደር አዝማሪ ከእነዚህ በላይ የግጥም ቅኔዎች ማሽሞንሞን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ይህን ግጥም በሕሊናችሁ በማሲንቆ አጃቢነትና በመረዋ የቡርቧክስ አዝማሪ ድምጽ ስሙት (ቡርቧክስ ከጎንደር ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ያክል የሚርቅ ማክሰኝት የምትሰኝ ከተማ ወደ በለሳ መውጫ በኩል ያለ የገጠር ቀበሌ ሲሆን የበርካታ አዝማሪዎች ቀዬ ነው)፡፡

ኧረ አገሬ ጎንደር ሸንበቆው ማማሩ፣

አገሬ ወስከንቢት ሸንበቆው ማማሩ፤

ኧረ አገሬ ቋራ፣ መተማ አርማጭሆ ሸንበቆው ማማሩ

አገሬ ወልቃይት፣ ቃፍታና ኹመራ ሸንበቆው ማማሩ፣

ቆርጠው ቆርጠው ጣሉት ለም-አገር እያሉ!

አዝማሪው አገሩን በሸንበቆ መስሎ ለም ለም የሆነው ሁሉ ተቆርጦ አንድም ለሱዳን አሊያም ለታላቋ የትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ መወሰዱን በቁጭት ነው በቅኔ የሚገልጸው፡፡ የሆነው ሆኖ በዚያ ቀን አብዛኛው በበካፋ የባህል ቤት ሲዘፈን ያመሸው ስለወልቃይት ነው፡፡ አንድ ራሰ በራ ድምጸ መረዋ አዝማሪ አለ፡፡ የድምጹ ነገር ወፍ ከሰማይ ያወርዳል፤ ወይንም በአገራችን አባባል ነብር ይጠራል፡፡ የፋሲል ደመወዝን ‹‹አረሱት መተማ፣ አረሱት ኹመራን የውም የእኛን እጣ፣ እነርሱ ምን ያርጉ ከእኛ ሰው ሲታጣ›› ያለ ጊዜ የምድር ቤት ውስጥ ያለው አዳራሽ በጩኸት ተናወጠ፡፡ መቼም በጩኸት ከኢያሪኮ ከተማ ውጭ የፈረሰ ግንብ አልሰማሁም እንጅ ያን እለት የነበረው ጩኸት ከዚህ ላይ ለመግለጽ ቃላት መፈለግ ግድ ይለኛል፡፡

አዝማሪው ያዘምራል፡፡ እንዲህ በማለት

ኧረ አገሬ ጎንደር ሰሜን ጃናሞራ ወልቃይት ጠገዴ፣

ለራበው እንጀራ ለጠገበው ጓንዴ!

ወደ መድረክ ሰው ሁሉ መቶ ብር መወርወር ጀመረ፡፡ በዚያ ምሽት ቤቱን አይቶ የማያውቅ እንግዳ ሰው ቢገባ የቤቱ ሕግ መስሎት መቶ ብር እንደሚወረውር በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ፡፡ መድረክ አካበቢ ወደ አዝማሪው ስመለከት ውር ውር የሚሉ አረንጓዴ ቢራቢሮዎች ባለማሲንቆውን ሸፍነውታል፡፡ አዎ ቢራቢሮዎች አይደሉም፤ የባለ መቶ ብር ኖቶች እንጅ፡፡ ከዚህ ቤት ውስጥ የታመቀ ብሶት ፈንድቷል፡፡ የተጠራቀመ ቁጭት ፈሷል፡፡ ወጣቱ ደሙ ፈልቷል፡፡ ባርነትን በቃህ የሚል ይመስላል፡፡ ማንም ይህን የተናገረ የለም፤ እኔ ግን እያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ ያለውን ስሜት አንብቤዋለሁ፡፡ ሊመርጅ የገባው የደህነንቱም ሰው ስሜት ቢሆንም!!

እስኪ አንድ ሰው እስክስታ እየመታ ሲያነባ፣ ግማሽ ፊቱ የብርሃን ጸዳል ወርሶት ግማሹ ግን የዳመነ ሲሆን፣ ውስጡን በነገር ሞልቶ መተንፈስ አልችል ሲል፣ ሁለት ፍጹም ተቃራኒ ስሜቶች በአካላቱ ላይ ሲነበቡበት ያያችሁት ሰው አለ? ወይስ ይህ ስሜት ገጥሟችሁ ያውቃል? እኔ በዚያ ቤት ውስጥና በዚያ ሰዓት ያየሁት ግን ይህ ነው፡፡ ቤቱን ሁለት ፍጹም ተቃራኒ መናፍስት ወርሰውት አምሽተዋል፡፡

የሚቀጥል

Ethiopia and Sudan set to launch joint military operation

Sudan Tribune By Tesfa-Alem Tekle (ADDIS ABABA) – Ethiopia’s ministry of defence announced on Wednesday that it had reached an agreement with its Sudanese counterpart to establish a joint military force which would operate under the same command. Forces will be deployed on eight fronts along the two countries’ common border with the aim of

The post Ethiopia and Sudan set to launch joint military operation appeared first on 6KILO.com.

Border Demarcation Ends Sudan-Ethiopia Border Chaos, stated Governor of Gedarif

Sudan Vision Daily

image

The security chaos witnessed on the Sudan-Ethiopia border can be solved by border demarcation, stated Governor of Gedarif, Al-Daw Al-Mahi, on Saturday.

During a visit to territorial localities, Al-Mahi stated to Sudan Media Center (SMC) that the situation is stable on the Sudan-Ethiopia borderline, asserting his government’s commitment to protecting citizens as well as securing the upcoming agricultural season. 

Al-Mahi explained that the process of securing borders is the direct responsibility of the federal government. “The federal government has carried out tangible efforts to demarcate Sudan-Ethiopia borders,” concluded Al-Mahi. 

የሸፍጥ ክርክር የሃሰት ክምር የታሪክን እውነታ አይቀይርም! (ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ)

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ/ም ( February 22, 2014 )

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ PDF EBAC-Feb-22-2014

I. መግቢያ:

የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ/ም የወያኔ/ኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአገር-ውስጥ ጋዘጤኞች በሰጡት መግለጫ ላይ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በድፍረት የሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴን ብቻ አይደለም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ያሳዘነና ያሳፈረ ሆኖ አግኝተነዋል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እግር የተተኩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቡት የመንግሥት ሥልጣንን ብቻ ሣይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከበሬታ-አልባነትንም በሚመስል መልክ ነው ይህንን በጣም የተምታታ፤ በተቃርኖዎች የተሞላና በእጅጉ ኃላፊነት-የጎደለው ጋዜጣዊ-መግለጫ የሰጡት።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባደረገው ያላሰለሰ ክትትል የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር የሕዝብን መሠረታዊ-ሉዓላዊነት በሚዳፈርና ዘለቄታዊ ጥቅሙን ለባዕድ አሣልፎ በሚሰጥ ሁኔታ እየሸረበ ያለውን ደባና እየፈጸመ ያለውን አሣፋሪ ድርጊት በተገቢ ጥናትና በጠራ-መረጃ ላይ ተመሥርቶ በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎች እንዲሁም በልዩ-ልዩ መገናኛ-ብዙኃን አማካይነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎችና ልዩ-ልዩ ተቋማት፤ ለሱዳን መንግሥትና ለዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ሲያሳውቅ መቆየቱ ይታወቃል። የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ግን አሁንም በዚህ የአገር ድንበርን በሚያክል ከባድ ጉዳይ ላይ ከዋናው ባለ-ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የጀመሩትን እኩይ ተግባር እየገፉበት አንደሆነ ከራሣችው አንደበት እየሰማን ነው።

II. የመግለጫው ዓላማ፤

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በሚከተሉት ምክንያቶች ከላይ የተጠቀሰውን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር በተመለከተ ይህንን መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።

ሀ). ከማንኛውም አገርና መንግሥት መሪ በተለይም የውጭ ግንኙንትን በተመለከተ የሚሰነዘር አስተያየትም ሆነ የሚሰጥ መግለጫ የአገር አቋም ተደርጎ የሚወሰድና በዋቢነትም የመጠቀስ መዘዝን ያዘለ በመሆኑ በዝምታ ሊታለፍም ሆነ ‘አጉል-መዘላበድ’ ተደርጎ ችላ ሊባል የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ፤

ለ). በዚህ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ እየፈጸመ ባለው በአገር-ክህደት የሚያስጠይቅ፤ ሕዝብን የናቀ የድፍረት አርምጃና ሕገ-ወጥ ድርጊት አገራችን ኢትዮጵያ አንጡራ መሬቷ ለባዕድ አሣልፎ እየተሰጠ መሆኑ ምንም ዓይነት ተቀባይነትም ሆነ አግባብነት የሌለው ብቻ ሣይሆን የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጉዳይና ሁሉም በግልጥ ሊረዳው የሚገባ መሆኑን ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ መግልጫዎች የሰጠነበት ቢሆንም አሁንም በድጋሜ ማሳሰቡ አስፈላጊ ስለሆነ፤

ሐ). አፄ ቴዎድሮስ፤ ንጉሥ ተክለ-ኃይማኖትና አፄ ዮሐንስን የመሳሰሉ ታላላቅ መሪዎች እየታገሉና ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አስከብረውት የቆየውንና በአካባቢው ሕዝብ የመረረ ተጋድሎ ታፍሮና ተጠብቆ የኖረውን የሱዳን ወሰን በድብቅ ስምምነት ለባዕድ አሣልፎ ለመስጠት የሚደረግ ሕገ-ወጥ ውል ውሎ-አድሮ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ የማይታይ ከመሆኑም በላይ፤ ይህንን በመሰለ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ በተፈጸመ ውል ድንበር ለማካለል የሚወሰድ እርምጃ ሁለቱን እህትማማች አገሮች ወደ-አይቀሬ ጦርነት የሚወስድና ይህም ኢትዮጵያና ሱዳን በመልካም ጉርብትና መርኅ ተከባብረው እንዳይኖሩ፤ የውስጥ ሰላማቸውንና እድገታቸውን ወደሚያደናቅፍ ያላስፈላጊ ችግር ውስጥ ከማስገባት አልፎ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ጠንቅ እንደሚሆን ሁሉም ሊያውቀው ስለሚገባ፤

መ). የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በሱዳን በኩል ያለውን የአገር ወሰን በተመለከተ በድብቅ የሚያደርጉትን የክህደት ተግባር በወቅቱ ማጋለጥና ማክሸፍ ተገቢና የማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚያሳስበውና የሚታገለው፤ ይህ ሕገ-ወጥ እርምጃ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ድንበሮቻችን እንዲደፈሩና አገራችን ኢትዮጵያ አንጡራ መሬቶቿን በተመሣሣይ ሁኔታ እንድታጣ በር-ከፋች ማስረጃ ሊሆን እንዳይችል ለማድረግም ጭምር ስለሆነ፤

ሠ). ይህንን ድብቅ ሴራ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትክክል እንዲያውቀውና በተለይም የአገሩን ዳር-ድንበር የማስከበር ኃላፊነት ያለበት የአገሪቱ የመከላከያ ኃይልና የአገር-ደኅንነት ክፍል አባላት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች አሳፋሪ በሆነ መልኩ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርተው የአገራቸውን አንጡራ መሬት ለባዕድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያደርጉትን የአገር-ክህደት ተግባር በትክክል ተረድተው ከሕዝባቸው ጎን አንዲቆሙና የአገራቸውን ዘለቄታዊ-ጥቅም የማስከበር መሠረታዊ የሙያ፤ የተቋምና የዜግነት ግዴታቸውን አንዲወጡ ማሳሰቡ አስፈላጊ በመሆኑ፤

ረ). በአገራችን የሥርዓት-ለውጥ እንዲኖር የሚታገሉ ድርጅቶች ለዚህ ዓብይ አገራዊ ጉዳይ የተባበረ ምላሽ ለመስጠት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በአገራዊ አንድነት መንፈስና በተቀናበረ ሁኔታ እንዲሆን ለማሳሰብ፤…ነው።

III.  ጭብጦች፤

ሀ.) በአቶ ኃይለማርያም ደሳልኝ  / ኢሕአዴግ በኩል፤

1ኛ) አቶ ኃይለማርያም በዚህ መግለጫቸው ከእሳቸው በፊት የነበሩት የወያኔ/ኢሕአዴግ ጠቅላይ-ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓም የሕዝብ-ተወካዮች ምክር-ቤት ፊት ቀርበው ምንም ዓይነት ታሪካዊ ማረጋገጫ ሳይኖራቸውና ያለ-አንዳች ሃፍረት ያሉትን በመድገም ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሁሉም የሻለቃ ግዌንን መሥመር እንደተቀበሉና እንደተስማሙ፤

2ኛ) የእሳቸውም መንግሥት ወያኔ/ኢሕአዴግ ይህንኑ የግዌን የወሰን ክለላ መሥመር እንደሚቀበል፤ በተግባር የመተርጎም ግዴታ እንዳለባቸውና ለዚህም ዝግጁ መሆናቸውን፤

3ኛ) ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት አንድም የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ እንደሌለና ወደፊትም ሊኖር እንደማይችል፤

4ኛ) የሱዳንን ታጋሽነት በማወደስና የኢትዮጵያን ‘የተስፋፊነት’ አቋም በማውገዝ፤ ሃቁን በመካድና ታሪክን በማጣመም አሁን ሱዳን ይገባኛል የምትለውና የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥትም ለማስረከብ የተዘጋጀው መሬት ቀደም-ሲል በሱዳን ይዞታ ሥር የነበረና የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባራክ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት በተካሄደው የግድያ ሙከራ ሳቢያ በኢትዮጵያና በሱዳን መኻል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ‘ሱዳኖች የለቀቁትን መሬት ኢትዮጵውያን ገበሬዎች አልፈው ሲያርሱት የነበረውን’ አንደሆነ፤

5ኛ) በሁለቱ አገሮች መኻል ያሉ ልዩ-ልዩ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሁለቱም አገሮች የተሰየሙ ኮሚቴዎች በቋሚነት እየተገናኙ ምክክር ከማድረግና ውሎችን ከመዋዋል ውጪ በአሁኑ ጊዜ የተከለለ መሬት እንደሌለ፤

6ኛ) ይህንን ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት አሳልፋ ሰጠች የሚለው ‘አሉባልታ’ በአገሪቱ በየአምስት ዓመት የሚደረገውን የምርጫ ወቅት እየጠበቀ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በወያኔ/ኢሕአዴግ ላይ የሚነዛ ወሬ እንደሆነ፤…

የእሣቸውንና የመንግሥታቸውን አቋም ሲያሣውቁ፤ በአጠቃላይ የአቶ ኃይለማርያም ደሳልኝ መግለጫ ይዘት ከአሁን በፊት አቶ መለስ ታሪክን በመከለስና ሃቁን በማድበስብስ የተናገሩትን በአዲስ መልክ በመድገም የኢትዮጵያን አንጡራ መሬት ለሱዳን አሣልፎ ለመስጠት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ያላቸውን አቋምና እምነት፤ ይህንንም በተግባር ለመተርጎም የደረሱበትን ውሳኔ ይፋ ያደረገና በኢትዮጵያ ላይ ምስክርነት የሰጠ ሆኖ አግኝተነዋል።

ለ.) በኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል

1ኛ) የአውሮጳ ቅኝ-ገዥዎች ያለ-አፍሪቃውያን ተሣትፎና ይሁንታ የአፍሪቃን ምድር እንዳሻችው ሲቀራመቱ በነበረበት ወቅት ሱዳንን ከግብፅ ጨምራ ትገዛ የነበረችው ቅኝ-ገዠዋ እንግሊዝ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት ከነበሩት ብልኁ መሪ አፄ ምኒልክ ጋር ድርድርና ውል ማድረጋቸው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።

አፄ ምኒልክም ሆኑ ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ከእነዚህ አውሮጳውያን ጋር ውል ሲዋዋሉና ሲደራደሩ በእነዚህ ባዕዳን የተውተበተቡ ብዙ ሴራዎችን እያከሸፉና የአገራቸውን ጥቅም ለአፍታም አሣልፈው ሳይሰጡ፤ አገራዊ ኃላፊነታቸውንና የመሪነት ግዴታዎቻቸውን በሚገባ የሚወጡ እንደነበር በኩራት የሚዘከር ነው።

በአንድ ወቅት አፄ ዮሐንስ አራተኛ “ምጥዋን ለጣሊያኖች አልሰጠኋቸውም፤ እንግሊዞች ናቸው የሰጧቸው፤ ምጥዋ የኢትዮጵያ ነው። እኔ በአግባቡ የኢትዮጵያ የሆነውን ማንኛውንም ግዛት የመተው ፍላጎትም ሆነ ሥልጣኑም የለኝም’’ ሲሉ እንዳረጋገጡት ሁሉ፤ በአገር-ወዳድነታቸው የታወቁት የኢትዮጵያ መሪዎች ከፈጣሪ በታች ጠያቂ የሌለባቸውና ምንም ነገር ለማድረግ ሙሉ-ሥልጣን የነበራቸው ቢሆንም አንኳ የሕዝብንና የአገርን ጥቅም አሣልፈው ያልሰጡ ብቻ ሣይሆን ጥንት የኢትዮጵያ ግዛቶች የነበሩና በልዩ-ልዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ይዞታ ውጪ የሆኑትን ለማስመልስ ያለ-መታከት የሚጥሩ፤ በዚህ ጥረትም ሕይዎታቸውን መስዋዕት ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።

አገራችን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ወሰን በተመለከተ አፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተዋዋሉት ያ ውል ግን አሁን የኢሕአዴግ መሪዎች የሚሉትንና አጣምመው የሚያቀርቡትን ሻለቃ ግዌን የተባለ የእንግሊዝ መኮንን ያለኢትዮጵያ ተሣትፎና እውቅና፤ በራሱ ፈቃድዓይንባወጣ አድሎዓዊነትብቻውን አሰመርኩት የሚለውን መስመር ፈጽሞ የሚመለክት እንዳልሆነ በተገቢ ግልጥ መሆን ይኖርበታል። ‘የግዌን መስመር’ የተባለውን ይህ የተናጠል ውሳኔ አንድም የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ መሪ እንኳን ሊገዛበት ሕጋዊ እውቅና የሰጠበትም ሆነ ትክክል ነው ብሎ አምኖ የተቀበለበት ጊዜ የለም። እንግዲህ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በግልጥ እያምታቱ ያሉት አፄ ምኒልክ አገራቸው ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል ያለውን ድንበሯን በተመለከተ ከእንግሊዝ ጋር ያድረጉትን ስምምነትና ከዚያ በኋላ ግዌን ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ብቻውን አካልያለሁ የሚለውንና በኢትዮጵያ በኩል ምናልባት ከአቶ መለስና ከምትካቸው ከአቶ ኃይለማርያም የተዛባና ሃቁን ያወናገረ ምስክርነት በስተቀር ምንም ዓይነት ሕጋዊ-ተቀባይነትም ሆነ አስገዳጅነት የሌለውን የአንድ-ወገን ውሳኔ ነው።

‘የግዌን መስመር’ የተባለውን ቅድመ-ወያኔ/ኢሕአዴግ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት መቸውንም ያልተቀበሉት፤ ኢትዮጵያም ልታከብረውና መቀበል ልትገደድበት የማትችል በመሆኑ፤ ይህንን በተለየ መልኩ ለማቅረብ የሚከጅሉ መሠረታዊ በሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊና አገራዊ ጥቅም ላይ ከሚዘምቱ ባዕዳን ተለይተው ሊታዩ የማይችሉና በአገር-ክህደት ተግባር የሚያስጠይቃቸው እንደሆነ ለሁሉም ግልጥ መሆን ይኖርበታል።

2ኛ) አቶ ኃይለማርያም በዚህ መግለጫቸው የተረኩት ሌላው በጣም አስገራሚና መሠረተ-ቢስ አባባል ደግሞ በኢትዮጵያና በሱዳን መኻል እ.አ.አ. በ1996 ዓም በተፈጠረው ግጭት ሣቢያ ሱዳኖች የለቀቁትን መሬት ኢትዮጵያውያን ድንበር ዘልለው ሲያርሱ እንደነበርና ይህ መሬት የሱዳን በመሆኑ ሊመለስላቸው እንደሚገባ መንግሥታቸው እንደሚያምንበት፤ ይህንንም ተቀብሎ በተግባር ከመፈጸም ወደ-ኋላ እንደማይል የሚለው ህቶት ነው።

ሃቁን ገልብጦ ለመረዳት ካልተፈለገ በስተቀር እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ መሆኑ ግልጥ ነው። በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የተያዘ የሱዳን መሬት የለም። እንደሚታወቀው በአፄ ኃይለ-ሥላሴ መንግሥትም ቢሆን ኢትዮጵያ በሱዳን ወሰኗ በኩል ጎላ-ብለው የሚታዩ የጦር-ሠፈሮች አልነበሯትም። በደርግ ጊዜም ቢሆን በዋናነት የውስጥ ተቃዋሚዎችን ለመፋለም ካልሆነ በስተቀር ለድንበር ጥበቃ የሚበቃ ሠራዊት በዚህ የአገሪቱ መሥመር አልነበረም። ድንበሩ ተከብሮ የኖረውና በሱዳኖች በኩል ይደረጉ የነበሩ አንዳንድ ድንበር-ዘለል መተናኮሶችን ሲከላከልና ሲያከሽፍ የኖረው የአካባቢው አገር-ወዳድ ሕዝብ እንደነበር ይታወቃል። በደርግ ጊዜም በተለይ በጎንደር ክፍለ-አገር ባለው ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት አካባቢ ከሕዝቡ በተጨማሪ የኢዴኅ (ኢዲዩ)፤ የኢሕአፓ፤ የአገር-ወዳድ ድርጅት፤ የከፋኝ አርበኞች ድርጅት፤ ወዘተ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱ ስለነበር፤ አሁን የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ‘ቀድሞ የሱዳን ይዞታ የነበረና በኋላ ግን የኢትዮጵያ አራሾች የያዙት መሬት’ ብለው በድፍረት የሚናገሩት ከኢትዮጵያውያን ይዞታና ቁጥጥር-ውጭ ያልነበረ ነው። ደርግ እየተሸነፈ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲያመራ ቀደም-ሲል ሕዝባቸውን እያስተባበሩ ድንበራቸውን ያስከብሩ የነበሩ የአካባቢው መሪዎች በሞት እየተለዩና ድንበር-ጠባቂዎችም የተለመደ የድንበር-ማስከበር ሥራቸውን መሥራት ያልቻሉበት ጊዜ ስለነበር፤ እንዲሁም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ታጣቂ-ኃይሎች በልዩ-ልዩ ምክንያቶች በአካባቢው ያልነበሩበት ሁኔታ በመከሰቱ፤ ሱዳኖች ይህንን የተፈጠረ ክፍተት ተጠቅመው ድንበር እያለፉ የኢትዮጵያን መሬት መያዝና ጦር ማስፈራቸው ይታወቃል። እግር-በእግርም የሱዳን ገበሬዎችና ሃብታሞች ይህንኑ በሕገ-ወጥ መንገድና በጉልበት የተያዘ የኢትዮጵያ መሬት ማረስና ማሳረስ፤ ጫካውንም እንደፈለጉ ማውደምና መዝረፋቸው ግልጥ ነው። የአካባቢው ሕዝብ ይህንን የሱዳን ድፍረት ለመቋቋም ለአዲሶቹ ገዥዎች (ለወያኔ/ኢሕአዴግ) አቤቱታ በማቅረብ ጭምር የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ አልተቆጠበም።

“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” አንዲሉ ነውና ምናልባትም ይህንን ጉዳይ በትክክል ግልጥ ለማድረግ በወቅቱ የአዲሱ መንግሥት የመከላከያ-ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ግንቦት 23 ቀን 2000 ዓ/ም በወጣው ‘አዲስ ነገር’ ጋዜጣ ላይ ያሠፈሩትን ሃቅ በዋቢነት መጥቀሱ አስፈላጊ ነው። አቶ ስዬ የተባለውን የጽሑፍ ምስክርነት የሰጡት ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ/ም አቶ መለስ የሱዳንን የድንበር ጉዳይ በተመለከተ ሕዝብ-ተወካዮች ምክር-ቤት ፊት ቀርበው ለሰጡት የተዛባ ዘገባ ምላሽ ነው። አቶ ስዬ በዚህ ጽሑፋቸው ግልጥ ያደረጉት ነገር የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሣልፎ ለመስጠት በማስረጃነት ሊጠቀሙበት የሚሹትና እንደ-ምክንያት የሚያቀርቡት አንዱ ይህ አሁን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የደገሙትና ቀደም-ሲል አቶ መለስ ሃቁን ገልብጠው ያቀረቡት ለሱዳን ለመስጠት የወሰኑት ‘ቀደም-ሲል በሱዳን ይዞታ ሥር የነበረውንና በኋላ በግብፅ መሪ ላይ በተሰነዘረው የግድያ ሙከራ ሣቢያ ኢትዮጵያና ሱዳን መኻል የነበረው ግጭት በፈጠረው ክፍተት ኢትዮጵያውያን ድንበር ተሻግረው ያርሱት የነበረውንና ድሮም የሱዳን ይዞታ የነበረውን ነው’ የሚለውን የፈጠራ ትረካ ነው። አቶ ስዬ ስለዚሁ ጉዳይ በዚህ ጽሑፋቸው ያቀረቡትን በሰፊው እንጠቅሳለን።

“የሱዳን መንግሥት ይህንን የጥበቃ ኬላዎች ያለመኖር ሁኔታ በመጠቀም ሠራዊቱን ወደዚህ ቀጠና ማስገባቱን ቀጠለ። ሱዳናውያን አራሾች የሠራዊታቸውን ኮቴ እየተከተሉ መጠጋት ጀመሩ። ባለቤት የሌለው መሬት አገኘን ብለው ደኑን ማጥፋት፤ የእርሻ መሬቱን እንዳሻቸው መያዝ ቀጠሉ። ይባስ ብለው በእርሻ ሥራ መቋቋም የጀመሩትን ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መተናኮልና መጋፋት ጀመሩ። ሁኔታው አየባሰበት በመሄዱ ውሱን የመከላከያ ኃይል በዚሁ አካባቢ በማስፈር ቀስ በቀስ ይህንኑ ማጠናከር ጀመርን። ሠራዊቱ ይህን በአራሾች ላይ የሚደርሰውን በደል እና በዓይናችን ፊት የሚደርሰውን ውድመት መቃወም ጀመረ። በአካባቢው የተመደበው የመከላከያ ሠራዊታችን አዛዥ የጽሑፍ መልእክቱን አስይዞ አቻው ወደሆነው የሱዳን ጦር አዛዥ አንድ የመላክተኛ ጓድ ይልካል። የተላከው ጓድ የተደረገለት አቀባበል የወዳጅ ሠራዊት አቀባበል አልነበረም። ኑ ብለው ተቀብለው ትጥቃችውን አስፈትተው አረዷቸው። ይህ ድፍረትና ጭካኔ እንደተፈጸመ ሠራዊታችን አይምሬ የአጸፋ እርምጃ ወስዶ በአካባቢው የነበረው ጦር እንደወጣ ቀረ። እኔ በኃላፊነት እስከነበርኩበት ጊዜ ድረስ ሱዳኖች ወደዚህ እካባቢ ተተኪ ሠራዊት አላኩም። አቶ መለስ ሠራዊታችን በ1995/1996 አካባቢ የወሰደው ማጥቃት ብሎ የገለጸው ይህንኑ የአጸፋ እርምጃ ነው። ይህንን አካባቢ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ምክንያት በእጃችን የገባ የእኛ ያልሆነ መሬት አድርጎ ማቅረቡ ግን ትክክል አይደለም። የሱዳን ወታደሮች እና እነርሱን ተከትለው የመጡት የሱዳን አራሾች ወደዚህ ቀጠና የመጠጋታቸው ታሪክ ከፍ ብሎ ከገለጽኩት የነገሮች አንድነት ጋር የተያያዘ ነውና ድንበር ሳይካለል በፊት እንደዚህ ብሎ ፍርድ መስጠት አይገባውም ነበር።  አስቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ እየመሰከረ ነው።”

ሲሉ ስለሁኔታው ምስክርነታቸውንና ትዝብታቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ አሳውቀዋል።

3ኛ) የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ለሰባት ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሣይሆን እራሱ ከሚቆጣጥረው ፓርላማ ጀርባ በድብቅ ያቋቋማቸው ‘የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን’ እና ‘የኢትዮጵያና የሱዳን የፖለቲካ ኮሚቴ’ የሚባሉ ሁለት ልዩ አካሎች መኖራቸውን ይፋ ያደረገው ይህን ድብቅ ሥራውን ማጋለጥ ከተቻለ በኋላ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ከሱዳን ጋር በእነዚህ ድብቅ አካሎች አማካይነት በየጊዜው ስለሚደራደራቸው ኢትዮጵያን የሚጎዱ ውሎችና ስለሚፈጽማቸው የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ተግባራት ማወቅ የቻለው በመንግሥት ስም ከተቀመጠው አካል ሣይሆን ጋፍኛ ከሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናትና ከእነሱው መገናኛ-ብዙኃን ነው። የዚህ ድብቅ ሴራ ተጠቃሚ የሆኑት ሱዳኖች ከለጋስ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በየጊዜው ስለተቸሯቸው የኢትዮጵያ መሬቶች የምስራቹን ለሕዝባቸው ቢያበስሩና በአንፃሩ ከሕዝብ ጀርባ ተደብቀው አገርን የሚጎዳ የክህደት ተግባር ላይ የተሰማሩት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች መሰሪ ሥራቸው እንዳይታወቅ ለመደበቅ ቢሞክሩ፤ ያ ደግሞ ሳያስቡት ይፋ ሲሆን ምንም ተቀባይነትም ይሁን ታሪካዊ እውነታ የሌላቸው የሃሰት ማስረጃዎችን ለመደርደር ቢማስኑ ላያስገርም ይችላል። የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው ግን የባዕዳንን ተደጋጋሚ የቀጥታ ወረራዎች ጭምር ተቋቁማና ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ አገራችን እንመራታለን በሚሉ በራሧ ልጆች ችሮታ ድንበሯ መደፈሩና አንጡራ መሬቷን እንድታጣ መደረጉ ነው።

እንደ ሱዳን ባለ-ሥልጣኖች ቀጥተኛ ዘገባ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ድንበር ለመካለል ከወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን ብቻ ሣይሆን ቋሚ የወሰን ምልክቶችን ለማስቀመጥ ቀኖች መቆረጣቸው፤ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚጠይቀው ወጪ ሱዳን ሁለት-ሦስተኛውን ለመሸፈን ፈቃደኛና ዝግጁ መሆኗን፤ እንዲያውም ሥራው ከወዲሁ መጀመሩን ጭምር ያስረዳል። ይህ እውነታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ሲታወቅ ብቻ በአብዛኛው ጉዳዩን ለማስተባበል ሲባል አልፎ-አልፎ በወያኔ/ኢሕአዴግ የውጭ-ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚሰጡ መግለጫዎችና አሁን አቶ ኃይለማርያም ከሚናገሯቸው የተምታቱ ንግግሮች መረዳት የሚቻለው ቢያንስ በሱዳን በኩል የሚቀርቡ ዘገባዎችን ሃሰትነት በአስተማማኝ የሚያረጋግጡ አይደሉም። አንዲያውም እውነታውን ይበልጥ የሚያጋልጡ ሆነው ይገኛሉ።

4ኛ) ከአሁን በፊት ኮሚቴአችን ባወጣቸው መግለጫዎች እንዳሳወቀው ሁሉ፤ አቶ መለስ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ ም ፓርላማ ቀርበው ‘አንድም የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ የለም’ ብለው በድፍረት ሲናገሩ ልክ ከአንድ ወር በፊት (በሚያዝያ 13 ቀን) ድንበር ተሻግሮ በመጣ የሱዳን ጦር በቋራ ወረዳ ውስጥ ነፍስ-ገበያ ከተባለ የእርሻ ሥፍራ 34 ኢትዮጵያውያን ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎና ተዘርፎ እነሱም ታግተው ወደ ሱዳን ተወስደው መታሰራቸው እንኳ ጥቂትም የወገናዊነት መቆርቆር ቀርቶ ሰብዓዊ ስሜት አልታየባቸውም። ይበልጥ ስሜታቸውን የነካውና የከነከናቸው ሱዳኖች ያሳዩት ታጋሽነት (ያውም የኢትዮጵያን መሬት ለመውሰድ) እንደሆነ በአንደበታቸው ገልጠውታል። በጣልያን ወራሪዎች የተፈጸመው ልዩ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ ምናልባትም እነ-ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን አፍኖ ከአገራቸው ከኢትዮጵያ ወደ-እንግሊዝ ከወሰደው በናፒር የተመራው የእንግሊዝ የባዕድ ጦር ወዲህ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በባዕድ ወራሪ ጦር ከአገራቸው ታፍነው ወደ-ባዕድ አገር ተወስደው የታሠሩት በዘመነ-ወያኔ/ኢሕአዴግ ብቻ ነው።

አሁንም ኢትዮጵያውያን አርሶ-አደሮች ከዘመን-ዘመን ከኢትዮጵያ ይዞታና ቀጥተኛ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከማያውቀው እርሻቸው እየተፈናቀሉና እየተነቀሉ መሆናቸው፤ ሱዳኖች በወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ሥልጣንና ችሮታ ተሰጥቶናል በሚሏቸው ሥፍራዎች ቁጥጥራቸውን ለማጠናከር እየተጣደፉ እንደሆነ የዓይን ምስክሮች እያረጋገጡት ያለ ጉዳይ መሆኑ ሊታውቅ ይገባል።

5ኛ) ስለ-አገር ድንበር ጉዳይ በማንኛውም ጊዜ ማንሳትና የሚከሰቱ ስጋቶችን መግለጥ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታና የፖለቲካ ድርጅቶችም መሠረታዊ ኃላፊነት መሆኑን የዘነጉት አቶ ኃይለማርያም፤ ይህንን የድንበር ጉዳይ የሚያነሱ ወገኖችን (በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶችን) ‘ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ እየተጠበቀ የሚቀርብ’ ተራ የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው ለማሣየት ዳድተዋል። ጉዳዩን በዚህ መልክ ለማቅርብ የፈለጉበት ምክንያት ግልጥ ነው። አንድም የጉዳዩን ክብደት አቅልሎ ለማሳየትና ሕዝብን ለማደናገር ሲሆን፤ በዋናነት ግን አሁንም በተለይ ጉዳዩ በአግባቡ ያሳሰባቸውና ሕዝብን ሊያነሳሱብን ይችላሉ ብለው የሚሰጉባቸውን ድርጅቶች ከወዲሁ ለማሸማቀቅ በማሰብ ነው። የሚገርመው ግን በአንድ አፋቸው ከሱዳን ጋር ያለውን ድብቅ ድርድር ላለፉት አሥራ-ሦስት ዓመታት ሁለት ኮሚቴዎችን አቋቁመውና በየጊዜው እየተገናኙ ሥራቸውን እየሠሩ እንደሆነ እራሣቸው እየተናገሩ፤ እዚያው-በዚያው ይህንን እነሱ እያደረግን ነው የሚሉትንና ያልካዱትን ከሕዝብ የተደበቀ ሥራ ‘ሕዝብ እያወቀው ይሠራ፤ የምታደርጉት የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረርና ሕገ-ወጥ ነው’ የሚሉ ወገኖችን ኃላፊነት-የተሞላበት አቤቱታ አምስት ዓመት ጠብቆ ከሚደረግና ውጤቱ አስቀድሞ ከተወሰነ የምርጫ ጨዋታ ጋር ለማያያዝ መሞከር ቢያንስ ተኣማኒነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም።

IV. ማጠቃለያ:

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳ ኮሚቴ አሁንም ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ያለው መልእክት አንድ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ንቃችሁ ከሱዳን መንግሥት ጋር በድብቅ የምታደርጉት ማንኛውም ውል ሕገወጥ እንደሆነ፤ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አሣልፎ የሚሰጥና እናንተንም በአገርክኅደት ተግባር የሚያስጠይቅ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ከወዲሁ ያስታውቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልመከረበት፤ ባላወቀውና ባላመነበት ድርድር የሚደረግን ውሳኔ በለከት-የለሽ ዕብሪትና በተራ-ማምታታት ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አገርን ለባሰ አደጋ ማጋለጥ እንደሆነና ለውስጥም ሆነ ለአካባቢ አለመረጋጋት ምንጭ እንደሚሆን ልትገነዘቡት ይገባል። ስለሆነም በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት ከመተግበር እንድትቆጠቡ እናሳስባለን።

የአገር-መከላከያ ክፍሎችና አባላት ለዚህ ዓብይ አገራዊ ጉዳይ የሚገባውን ክብደት ሰጥታችሁ ባዕዳን ድንበር ገፍተውና ተሻግረው በሕዝባችሁ ላይ ለሚደርስ ብሶትና ሰቆቃ የሚኖርባችሁን ሙያዊና የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ብሔራዊ ኃላፊነት አለባችሁ።

ለሥርዓት ለውጥ የቆማችሁና የምትታገሉ አገር-ወዳድና ዴሞክራት ድርጅቶች የአገር ድንበር ጉዳይ በቀላሉ የሚታይም ይሁን ለጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ የሚመነዘር ሣይሆን መሠረታዊ የብሔራዊ ክብርና የጋራ ኅልውና መርኅ ነውና ተባብራችሁና ሕዝባዊ ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ይህን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ የጋራ እንቅስቃሴዎቻችሁን እንድታጎለብቱ እናሳስባለን።

ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ አንዳስገነዘብነው ሁሉ ይህ ጉዳይ ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ወይም ለተወሰኑ ክፍሎች የሚተው ሣይሆን የሁሉም የጋራ አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ፤ ዞሮ-ዞሮ የዚህ አሣፋሪ ድርጊት ዕዳ ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመኻልህ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከትም፣ የጎሣ፣ የሐይማኖትም ይሁን የአካባቢ ልዩነት ሳታሣይ ወዳጅ ቀርቶ ጠላት በመሰከረልህ የተለመደ የአገር መውደድና የአንድነት መንፈስ የጋራ ድምፅህን እንድታሰማና በጋራ እንድትቆም ወገናዊ ጥሪያችንን በአክብሮት አናቀርባለን።

በኢትዮጵያ ላይ የሚሸረብ ደባ ይከሽፋል!

የኢትዮጵያ ዳር-ድንበር በሕዝቧ ኅብረትና አንድነት ተረጋግጦ ይቀጥላል!!

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!!

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ

ባሶንዳ በተባለችዉ የሱዳን ጠረፍ ከተማ 77 ኢትዮጵያዉያን ተገደሉ

ባሶንዳ በተባለችዉ የሱዳን ጠረፍ ከተማ 77 ኢትዮጵያዉያን ተገድለዋል ሲሉ ከጥቃቱ የተረፉ ኢትዮጵያዉያን ገለጹ::

ከመተማ ቀጥላ በምትገኘዉ ባሶንዳ በምትባለዉ የሱዳን ጠረፍ ከተማና አካባቢ በኢትዮጵያዉን ሽፍቶችና በሱዳን ሽፍቶች መካከል የተነሳዉን ግጭት ተከትሎ አራት ሱዳናዉያን በመሞታቸዉ ሳብያ ለብቀላ የተነሱት ሱዳናዉያን ታጣቂ ሐይላት ኢትዮጵያዉይንን በጅምላ እየገደሉ ነዉ አገር ወገን ይድረስልን ሲሉ ወደ ሱዳን በመተማ በኩል የገቡ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች እየተጣሩ ነዉ።

አራት ሱዳናዉያን ስለሞቱ በመቶ ኢትዮጵያዊ ነዉ የምንበቀለዉ ያሉት ሱዳናዉያን እስከ አሁን 77 ኢትዮጵያዉይንን መገደላቸዉን በኩራት ይናገራሉ ያሉት ኢትዮጵያዉያን የአብዛኛዎቹ ሟቾች መቃብር የማታወቅ መሆኑንም ይናገራሉ። በየጫካዉ የተገደሉ ኢትዮጵያዉያን አስክሬናቸዉ ለዱር አራዊት መወርወሩን የሚገልጹት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ሌላ 42 ኢትዮጵያዉያን የተቀበሩበት መቃበር መኖሩንም ይጠቁማሉ፤ ይህ መቃብር ግን ከሞቱት 77 ሰዎች ጋር የሚያገናኘዉ ነገር ይኑር አይኑር የሚያዉቁት ነገር እንደሌለም ያስረዳሉ ።

በህዳር 24/2006 የሱዳኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ አህመድ አልቀርዲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሱዳንና ኢትዮጵያ ያላቸዉን የድንበር ልዩነት አስወግደዉ መስማማታቸዉን ይፋ አድርገዋል። ይህንንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ወደ ሱዳን ለስራ ጉብኝት አቅንተዋል። የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኡመር ሐሰን አልበሽር ሁለቱ አገራት በጥበቃ፣በደህንንነት፣ ህገወጥ የሰዉና የ አደንዛዥ እጽ ዝዉዉርን ለመግታት መስማማታቸዉን ገልጸዋል። በሱዳኗ ባሶንዳ የኢትዮጵያዉያን በጅምላ መገደል ከዚሁ የደህንነት ስጋት ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ባይታወቅም ሱዳናን ኢትዮጵያ ግድያዉን ለማስቆም ምንም አይነት ጥረት እንዳላደረጉ ከጥቃቱ የተረፉ ኢትዮጵያዉያን ያስረዳሉ ።

በየካቲት 11/2006 ህወሃት የተመሰረተበትን 39ኛ አመት ለማክበር የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ልዩ የክብር እንግዳ ሆነዉ መቐሌ ድረስ መምጣታቸዉ ታዉቋል። የሁለቱ አገራት መሪዎች ስለ ቀድሞ ስማእታት ቢናገሩም ወደ ሱዳን በኢኮኖሚ ሳቢያ ተሰደዉ ስለሚሞቱት ኢትዮጵያዉያን ምንም ያሉት ነገር አልነበረም። በባሶንዳ ሱዳን ኢትዮጵያዉያን ነጥሎ የማጥቃቱ ዘመቻ እንደቀጠለ ነዉ! ኢትዮጵያዉያን ወገን ይድረስልን ሲሉም ይጣራሉ።

Source: ዋሽንግተን ዲሲ፤ የካቲት 14/2006 (ቢቢኤን )