ሚስት ነኝ ሚስት እፈልጋለሁ!

ሚስት ነኝ ሚስት እፈልጋለሁ
ባለታሪኳ
ትላንት ልብን ከሚያደክም የሶስት ሰዓት ስብሰባ በኋላ ለዓርባ አምስት ደቂቃ ያህል ነድቼ ነበር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ቤቴ የገባሁት፡፡ ባለቤቴን ከልጆቹ ጋር እየተጫወተ አገኘሁት፡፡
ቦርሳዬን ወርወር አድርጌ ‹‹እርቦኛል ራት እፈልጋለሁ፤›› አልኩኝ፡፡
ሞግዚቷ አንገቷን አቀረቀረች፡፡ ‹‹ምነው?›› አልኋት ገርሞኝ፡፡ ‹‹ሰራተኛዋ ሄዳለች፤ ራት አልተሰራም፡፡›› አለችኝ፡፡ መቼም የዚህ አገር የቤት ሰራተኛ እና የዚህ አገር ዋጋ ያለማስጠንቀቂያ ኾኖል የሚወጡት፡፡
ምን ራት ብቻ ጠዋት ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ይዘውት የሚሄዱትንም መስራት አለብኝ ለካ፡፡
ጓዳ ገብቼ ጉድ ጉድ ስል
ሞግዚቷ፣‹በርበሬ አልቋል፤› አለችኝ፡፡ በዚህ ብታበቃ ምን ነበረበት፡፡ በቤቱ ውስጥ ያላለቀ ነገር የለም፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? የቤት ሰራተኛ እንጂ የሰራተኛ ልብ መቅጠር አይቻል፡፡
ደመወዝ መጨመር እንጂ ህሊና መጨመር አይቻል፡፡
እየተነጫነጭኹም፣ እየተማረርኹም የምችለውን ያህል ማሰናዳቴን ቀጠልኹ፡፡ በመካከል ግን አንድ ሐሳብ መጣብኝ፡፡
ምግብ እንደሌለ ከታወቀ እኔን መጠበቅ ለምን አስፈለገ?
ባለቤቴ ወደ ጓዳው ገባ ብሎ ለምን ሰርቶ አልጠበቀኝም? ሁለታችንም ስራ ነው የዋልነው፡፡
ሁለታችንም ልጆቻችን በልተው ማደር እንዳለባቸው እናውቃለን፡፡
ሁለታችንም በጾታ እኩልነት እናምናለን፡፡
የሁለታችንም የትምህርት ደረጃ ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱ አንድ ብቻ ይመስለኛል እርሱ ባል እኔ ሚስት መሆናችን፡፡
ከእርሱ በላይ እንዲያውም እኔ ነኝ ስደክምና ስታክት የዋልኩት፡፡ እኔም እንደ እርሱ ሚስት ቢኖረኝ ምን አለበት ብዬ ተመኘሁ፡፡
ገንዘቤን በሙሉ ሰጥቻት በታማኝነት ቤቴን የምታስተዳድር፣ በርበሬውን፣ ሽሮውን መጥና፣ ደቁሳ፣ አዘጋጅታ፣ ጤፉን መርጣ፣ ገዝታ፣ አስፈጭታ፣ ቅቤውን አንጥራ፣ ቅመማ ቅመሙን መጥና፣ በቤቴ ውስጥ ምን ጎደለ ምን አለ ብዬ ሳልጨነቅ እንዲሁ ያለሐሳብ የምታኖረኝ ሚስት ብትኖረኝ እኔስ እጠላለኹ እንዴ?
የቤት ሰራተኞች እንኳን ከባሎች ይልቅ ሚስቶችን ይጠላሉ፡፡ ወጥተው እንኳን ሲሄዱ፣
‹‹እርሷ ናት እንጂ እርሳቸውማ የእግዜር ሰው ናቸው ከአፋቸው አንዲት ነገር አትወጣም፤››
ብለው ባሎችን ነው የሚያመሰግኗቸው፡፡ ጨቅጫቃ፣ ነገረኛ፣ ገብጋባ፣ በትንሹ የምንናገር ተደርገን የምንቆጠረው እኛ ሚስቶች ነን፡፡ ከእነርሱ ጋር ክፉ ደግ የምንነጋገረው እኛው ነን፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ጥርግርግ አድርጋ ወስዳ የምትጨቃጨቅልኝ፣ ስድቤን ወስዳ ምስጋናውን የምትሰጠኝ ሚስት ብትኖረኝ እኔስ እጠላለኹ እንዴ፡፡
በርበሬ ተራ፣ ሽንኩርት ተራ፣ ቅቤ ተራ፣ አትክልት ተራ፣ ምናለሽ ተራ ፣ እህል በረንዳ፣ ሸቀጥ ማከፋፈያ ሄዶ፣ ተከራክሮ እና መርጦ ለመግዛት የግድ ሚስት መኾንን ይጠይቃል?
አንዳንድ ጊዜኮ ይገርማችኋል ባሎች፡
በአስር 10 ብር የሚገዙትን ሚስቶች በአምስት 5 ብር፣
ባሎች 100 ብር የሚያወጡበትን ሚስቶች በ40 ብር፣
ባሎች 50 ብር የሚያወጡበትን እኛ በ20 ብር ገዝተን እንመጣለን?
ለምን? እነርሱ ግዴለሽ ስለሆኑ እና እኛ ስለምንጠነቀቅ?
ወይስ
እኛ ገብጋባ ኾነን እነርሱ ቸር ስለሆኑ?
ለመሸከም፣ ስራ መስራት እና ዕቃ ለመሸጥ የሚመጡ ሰዎች እንኳ፣
ከእኛ ከሚስቶች ይልቅ ከባሎች ጋር መነጋገርን ይመርጣሉ፡፡ እናም ዘወር ሲሉ፤ ሚስቲቱ ግግም አሉ እንጂ ባልየውስ ዓርፈው ነበር፡፡ ይሏችኋል፡፡ ይህን ስትሰሙ ባልኾናችሁ ‹‹ማረፍ›› አያምራችሁም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙ ባሎችኮ የቤታቸውን ሳሎን እና መኝታ ቤት እንጂ ጓዳውን አያውቁትም፡፡
አንጀት የሚልጠው እና ጨጓራ የሚያቆስለው ደግሞ ጓዳው ነው፡፡
ስራ ውላችሁ፤ደክሞችሁ ርቧችሁ፣ታክቷችሁ ወደ ጓዳ እንደ መግባት ያለ ቅጣት በትዳር ውስጥ የለም፡፡ አንዱ ተሰብሮ፣ ሌላው ተደፍቶ፣ ምግቡ ክፍቱን ተቀምጦ፣ ዕቃው ተደበላልቆ፣ ለዓመት የተባለው በስድስት ወር፣ ለወር የተባለው በሳምንት አልቆ፣ ጨው ስኳር ጋራ፣ ሩዝ ከክክ ጋራ ተደበላልቆ ስታገኙት እርር ድብን ትላላችኹ፡፡ አትተውት ነገር ቤታችሁ ነው፤ አትናገሩ ነገር ሰሚ እንጂ አድማጭ አታገኙም፡፡ በዚህ ጊዜ ነውኮ ባል መኾን የሚያምራችኹ፡፡
ሚስቴ ከቤት ሰራተኛዋ ጋር ስትጨቃጨቅ እና ስትጣላ፤ ይህ ለምን አለቀ፤ ይህ ወዴት ሄደ፤ ይህን ለምን አልተናገራችኹም፤ ይህን ማን ሰበረው ፤ ይኽኛው ወጥ ለምን ፍሪጅ ውስጥ አልገባም፤ ይኽኛው ለምን ተበላሸ፤ ለምን አልተቦካም፤ ለምን አልተጋገረም፤ ለምን አልተፈጨም፤ እያለች
ሚስቴ ስትከራከር እኔም ባል ኾኜ አትጨቃጨቂ በቃ ተያት በትንሽ በትልቁ መነታረክ ምን ያደርግልሻል ደመወዟን አትንኪባት እያልኩ መምከር ናፈቀኝ፡፡
ሌላው ቀርቶ
ከልጆች ጋር ብሉ አትብሉ፣
ልበሱ አትልበሱ፣
ታጠቡ አትታጠቡ፣ ይህን አድርጉ አታድርጉ ፣ ቅባት ተቀቡ አትቀቡ እያሉ መከራከር እና ሲብስም መጨቃጨቅ የሚስቶች ስራ ነው፡፡
እኔ ለምን አባቴን እንደ ወደድኹ አሁን ነው የገባኝ፡፡ የሚጨቀጭቀውን ድሮስ ማን ይወድዳል፡፡ ባሎች እንደሆነ መጫወቻ መግዛት፣ ከረሜላ እና ቸኮሌት ማምጣት፣ መዝናኛ መውሰድ እና ማጫወት ነው የሚችሉበት፡፡ ታዲያ የአሁን ዘመን ልጆች አባታቸውን ቢወድዱ ይፈረዳል፡፡ እኔም ልጆቼን የምትለብስ፣ የምታስጠና፣ የምታጥብ፣ ተከራክራም ይሁን ተጨቃጭቅ ልጆቼን የምታበላ ሚስት ብትኖረኝ ምናለ? እኔም ባል ኾኜ ልጆቼ ያለጭቅጭቅ የሚበሉትን ቸኮሌት እና አይስክሬም ብቻ እየዛኹ ልጆቼ በወደዱኝ፡፡
‹‹ጹድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ›› አለች እናቴ፡፡ ብቻዬን የወለድኋቸው ይመስል
ለልጆቼ ምን መጠጣት ፣ምን መብላት፣ ምን መልበስ እንዳለባቸው እንኳን የምወስነው እኔ ነኝ፡፡
ባሌማ መብላታቸውን እንጂ ምን እንደሚበሉ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ምንም ያህል ስራ ቢበዛብኝ ቤት ደውዬ ማን ምን እንደበላ ማን ምን መብላት እንዳለበት ለሞግዚቷ መመርያ መስጠት አለብኝ እኔ እኮ ነኝ ፡፡
ልጆቼን ሰውነታቸውን ነካክቼ
ማተኮሳቸውን እና መቀዝቀዛቸውን
በሰውነታቸው ላይ ለውጥ መኖሩን እና አለመኖሩን የማየው እንኳን እኔ ነኝ፡፡
አብረን ቤት ብንገባም እንኳን ዛሬ እንዴት ኾነው ዋሉ? የሚለው የስስት ጥያቄ ከእኔ ነው የሚመጣው፡፡ እና ይህን ሁሉ ሸክም ተሸክማ ያለ ሐሳብ እንድኖር የምታደርገኝ ሚስት ባገኝ መመረቅ አይደለም ትላላችኹ፡፡
ወልጄ ለምን አልጠየከኝም፣ ልቅሶዬ ላይ የእዝን እንጀራ ለምን አላመጣኽም ቡና አብረኽኝ ለምን አልጠጣኽም፣ ስትወጣ ለምን ሰላም አትለኝም፣ ለምን ልቅሶ ቤት ሄዶ፣ ጓዳ ገብቶ ወጥ አልሰራም፣
ሰርግ ቤት ተጠርቶ ለምን ስራ አላገዝንም? ብሎ ባልን የሚቀየመው አላጋጠመኝም፡፡
ልቅሶም ሰርግም ብቅ ብሎ ከታየ እንደ ትልቅ ውለታ ይቆጠርለታል፡፡ ሚስት ስትኮን ግን ብዙ ይጠበቅባችኋል፡፡ እናም አንዳንድ ጊዜ ሰርግ እና ልቅሶ ላይ ዕድር እና አራስ ቤት እኔን ኾና የምትጠይቅልኝ፣ የሚወሰደውን ወስዳ የሚሰራውን ሰርታ፣
የሚከፈለውን ከፍላ ውለታ የምትገባልኝ እኔም ሲመቸኝ ብቅ እያልኩ ኮራ ብዬ በኀዘንተኛው መካከል ጋቢዬን ለብሼ ከቻልኩም ካርታ ተጫውቼ፣ ሰርግ ላይ ከቻልኩ አስተናግጄ ካልቻልኩም እንደ አድባር መሀል ላይ ጉብ ብዬ ባል ኾኜ መመስገን አማረኝ፡፡
ሌላው ቀርቶ ባል በሚስት ቤተሰቦች ዘንድ ከሚያጋጥመው ማኀበራዊ ችግር ይልቅ ሚስቶች ከባል ዘመዶች የሚያጋጥማቸው ችግር ይብሳል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሚስት መኾን ብቻውን እንደ ነገረኛ፣ ሰው በቤቷ ለመቀበል እንደማትፈልግ ፣ አንደ ገብጋባ ያስቆጥራል፡፡
ምናልባትም ለቤቷ መልፋቷ ሳያንሳት በቤቷ ላይ ሌላ ሰው ሲያዝዝ እና ሲያላሽ ስለሚይናድዳት ሊሆን ይችላል፡፡
አንድ ሰውኮ በቤታችሁ ጥልቅ ብሎ ገብቶ ስልጣኑኑ ይወስድና ኃላፊነቱን የቆየ መጥፎ አመለካከት የመጣም ሊኾን ይችላል፡፡ በዚያም ተብሎ በዚህ ሚስት በባሏ ብቻ ሳይሆን በዘመዶቹም ለመወደድ የመጣር ተጨማሪ ስራ አለባት፡፡
ያለበለዚያ እርሱማ የእግዜር በግ ምኑን ያውቀዋል እርሷ ናት እንጂ ትባላላችኹ፡፡ አይ ሚስት መኾን በተለይማ ወይ የሚረዳ ወይ የሚረዳ ባል ካልተገኘ፡፡
አንዳንድ የስራ ባልደረቦቼ እገሊትኮ ባልዋ እንዴት የተባረከ መሰላችሁ፣ ገንዘቡን ሁሉ አምጥቶ ለርሷ ነው የሚይስረክባት፡፡ እንዲያውም ከርሷ ጠይቆ ነው የሚወስደው እያሉ ሲያመሰግኑ እሰማለኹ፡፡
በርግጥ ዋርካ በሌለበት እምቧጭም ዋርካ ነው፡፡ ግን ምናለ እኔም ደመወዜን በሙሉ አምጥቼ አስረክቤ፣ ስፈልግ ከእርሱ እየወሰድኩ ባሌ ቤቱን ባስተዳደረልኝ፡፡
እኔም ባል ሆኜ፣ ገንዘብ ብቻ ሰጥቼ የቀረው ነገር ሁሉ ተዘጋጅቶ በጠበቀኝ?
ባሎችኮ ቤታቸውም ገንዘብ ሰጥተው ምግብ ይበላሉ፣ ሆቴልም ገንዘብ ሰጥተው ምግብ ይበላሉ፡፡
ሚስት ስትሆኑ ግን ቤታችሁ ውስጥ በገንዘብ ብቻ ምግብ አታገኙም፡፡ ጉልበት እና ጨጓራችሁንም ካልጨመራችሁ በቀር፡፡
ይህን ሁሉ ሳብሰለስል ሳላስበው ሰዓቱ ነጉዷል ለካ፡፡ ስራዬን ጨርሼ ወደ ሳሎን ብቅ አልኩ፡፡ ልጆቼ ፈንግል አንደያዘው ደሮ እዚህም እዚያም ወድቀው ዕንቅልፍ ወስዷቸዋል፤ ባለቤቴም ሶፋው ላይ ጋደም ብሎ ያለሐሳብ ተኝቷል እርሱ ምን አለበት በደህና ጊዜ ባል ሆኗል፡፡
ከዚህ ምን እንማራለን
ባል ከሚስቱ የሚስትነትን እንጂ የእናትነትን ፍቅር አይፈልግም
ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለትዳር በቂ እውቀት ሳይኖራቸው ይጋባሉ፡፡ ሰው እየገጩ፣ ልጆቻቸውን እየገጩ፣ ሚስቱን እየገጨ፣ ባሏን እየገጨች፣እየተገጫጩ ነው የሚኖሩት፡፡ ስታያቸው ግን ጤነኞች ይመስላሉ፡፡
ሴትና ወንድ በአስተሳሰብ ደረጃ ይለያያሉ
መታየት ያለበት ነግር ቢኖር
ወንድ የሚባል ሰው አለ፤ሴት የምትባል ሰው መኖራቸው ነው፡ በግልጽ ይታያል
ወንድ የሚያስብበት መንገድ፣ሴትም የምታስበበት መንገድ አለ፡፡ ወንድ እንደ ወንድ፤ ሴትም እነደ ሴት የተሰጣቸው ማንነት አለ፡፡ ይህም ይመስለኛል ወንድ ሴትን አብሮ ያኖራቸው ነገር፡፡
ሁለቱም ተመሳሳይ ከሆኑ ምን ፍለጋ ነው የሚጣመሩት የተለያዩ አስተሳሰብ ስላላቸው ነው፡፡ አንድ የሚያደርጋቸው የአስተሳሰብ መጠን አለ በትክክል ወንድና ሴት የተለያየ የአስተሳሰብ መጠን አላቸው፡፡
ወንድ ልጅ መከበር ይፈልጋል፡ የኢትዮጵያዊም አውሮፓዊም ወንድ ይህን ይፈልጋል፡
ወንድ ልጅ ችግር ሲገጥመው የሚፈታበት የራሱ መንገድ አለ፡፡ ወንድ ልጅ ደግሞ ተፈጥሮው ጠባቂ ነው፡፡ በቤቱ ውስጥ ማገር የመሆንና ሁሉን የመጠበቅ ስጦታ ተሰጥቶታል፡፡
ሴት ልጅ ደግሞ በተፈጥሮዋ እንክብካቤ ትፈልጋለች፡ በቃ እንቁላል ነች፣ ንግስት ነች፣ ሴት መደመጥ በጣም ትፈልጋለች ይሄ ተፈጥሮዋ ነው፡
የማዳመጥና የመደመጥ ክህሎታቸው ተፈጠሯዊ ነው፡ ወንድ ልጅ ይህ ተፈጥሮ የለውም ፡፡ መረጃ ሲሰጥህ እንኳን ጠቅለል አደረጎ ነው፡፡
በዝርዝር የሚያስቀምጠው ነገር የለም፡፡ የተ ነበርክ ስትለው እዚህ ቦታ ነው የሚልህ፡፡ ሴቷ ግን እዚያ ሄጄ፣ እንትናን አግቼው እንትን ጋብዞኝ ፍቀረኛውም አብራው ነበረች መዓት ነግር ልትልህ ትችላለች፡፡
ሚስት እንደ ሚስት ባልም እንደ ባል አለመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ባል ከሚሰቱ የሚስትነትን እንጂ የእናትነትን ፍቅር አይፈልግም!

አስገድዶ መድፈር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአምስት ዓመታት በፊት በመምህሯ መደፈሯ የተገለፀ አንዲት ተማሪ ሁኔታዉን ለሚመለከተዉ አካል አቤት ብትልም እስካሁን መፍትሄ አማግኘቷ አነጋጋሪ እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአምስት ዓመታት በፊት በመምህሯ መደፈሯ የተገለፀ አንዲት ተማሪ ሁኔታዉን ለሚመለከተዉ አካል አቤት ብትልም እስካሁን መፍትሄ አማግኘቷ አነጋጋሪ እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል። በዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ተፈፀመ የተባለዉን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ጥርጣሬ ደብዛ ለማጥፋት ተጎጂዋ ሃኪም ቤት የታከመችበትን ማስረጃ ምግኘት እንዳልቻሉ አንድ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

http://www.dw.de/%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8C%88%E1%8B%B5%E1%8B%B6-%E1%88%98%E1%8B%B5%E1%8D%88%E1%88%AD-%E1%89%A0%E1%8C%8E%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%88%AD-%E1%8B%A9%E1%8A%92%E1%89%A8%E1%88%AD%E1%88%B2%E1%89%B2/a-16481900