ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ተከሰሱ

በየካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሸ ዞን ያሶ ወረዳ በተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ምክንያት የክልሉ መንግሥት፣ የፌደራል ሚኒስቴርና በድርጊቱ ተሳትፈዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱ ታወቀ፡፡

ለበርካታ ዓመታት ከኖሩበት አካባቢ ያለምንም ማስጠንቀቂያ 1,346 የሚሆኑ አባዎራዎችን ጨምሮ 3,240 ቤተሰቦቻቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ በወቅቱ ለምን እንዲፈናቀሉ እንደተደረገ፣ የተፈናቀሉትም ወደነበሩበት ቀዬ እንዲመለሱና ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው፣ አፈናቃዮቹም ለሕግ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡ የአማራ ተወላጆችም የተፈናቀሉት ኪራይ ሰብሳቢዎች በሠሩት ስህተት መሆኑን በመጠቆም በሕግ እንደሚጠየቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በግልጽ መናገራቸውም እንዲሁ፡፡

ነገር ግን የክልሉ መንሥትም ሆነ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ለተፈናቃዮቹ ካሳ መስጠትም ሆነ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ባለማድረጋቸውና በተጠርጣሪዎቹ ላይ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው፣ ሰማያዊ ፓርቲ በታዋቂው የሕግ ምሁር ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም አማካይነት ያቀረበው ክስ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ በክሱ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የክልሉ መንግሥትና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ሚያዝያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ቀርበው የተጠረጠሩበት ክስ እንደሚነበብላቸው ታውቋል፡፡

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ያሶ ወረዳ 3,240 የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸው እውነት መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር አረጋግጠው፣ ችግሩ የተፈጠረው በኪራይ ሰብሳቢዎች መሆኑን በመጠቆም፣ ሁሉም ወደ ነበሩበት ቀዬ እንዲመለሱ መደረጉን መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

%d bloggers like this: