ግንቦቶች ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው

By ግርማ ካሳ

image

የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን በኤርትራ ላይ ይፋ ያደረገዉን ሪፖርት በተመረኮዘ በቅርቡ በሰጠሁት አስተያየት ዙሪያና የመለስ ቱሩፋቶች የሚለዉን መጽፍ የጻፈ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበረ አቶ ኤርሚያ ፣ በርካታ ጊዜያት በኢሳት መቅረቡን ጠቅሼ፣ “ኢሳት የኤርሚያስ ሾው ሆነ እንዴ ?” የሚል ጥያቄ በማንሳቴ፣ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ በርካታ አስተያየቶች ቀርበዉልኛል። ስለኢሳትና ስለ አቶ ኤርምያስ ወደፊት የአቶ ኤርሚይስን መጽሃፍ ካነበብኩ በኋላ እመለስበታለሁ። አሁን ስለግንቦት ስብት ትንሽ ልበል።
ግንቦት ሰባትን የመሰረቱ ወገኖች ለምን ግንቦት ሰባትን እንደመሰረቱ አውቃለሁ። በወያኔ ትልቅ ግፍ የተፈጸመባቸውና የተናደዱ ፖለቲከኞች ናቸው። አቶ አንዳርጋቸው ጸጌ፣ ዝዋይ በዘጠና ሰባት ታስሮ በነበረ ጊዜ በሰደፍ አይኑን መተዉታል ፣ እሰከአሁን ድረስ አይኑ ላይ ችግር አለበት። በሚገባ ይገባኝል ንዴቱና ብሰጭቱ !!!!!!!!

ነገር ግን ንዴትና ብስጭት ብቻ አገርን ነጻ አያወጣም። በየአዲስ አመቱ ንግግር ማድረግ፣ በየሰብሰባው ትያትራዊ በሆነ መንገድ ሕዝቡ ጠንቅቆ የሚያወቀዉን የወያኔን ሐጢያት እየደጋገሙ መናገር ለዉጥ አያመጣም። ነገር ግን ሁሉንም ያገናዘበ፣ ዉጤታማነቱ በየጊዜው የሚፈተሽ፣ የሚጠቅም ስትራቴጂ ያስፈልጋል።
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ብዙ የሰራቸውና ያስመዘገባቸው ዉጤቶች አሉ። ለነጻነትና ለፍትህ በሚደረገው ትግል ዉስጥ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ከሻእቢያ ጋር ያለውን ግንኙነት መመርመር አለበት የሚል ጠንክራ እምነት አለኝ። ግንቦት ሰባትን ስተች፣ በድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች መካከል ጤናማ የሆነ ዉይይት እንዲኖር ለማበረታታትም ነው። አባላትና ደጋፊዎች በጭፍን መከተል አቁመው መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ ነው። ድርጅቱ ከተሳሳተ መንገዱ ተምልሶ ጥቅም በሚያመጥብት መንገድ እንዲሰማራ ግፊት ለማድረግ ነው።

እስቲ ትንሽ ከሃያ ሶስት አመታት በፊት ወደነበረው ሁኔታ ልመልሳችሁ። ሻእቢያ መጀመሪያ ሰሞን ከኢሕአፓ ጋር ወዳጅ ነበር። ኢሕአፓ አገር ቀፍ በመሆኑ፣ ፊቱን ወደ ሕወሃት አዞረ። ሕውሃትን አጠናከረ። ሕወሃት ትግራይን በተቆጣጠረ ጊዜ ወደ ደቡብ መዝለቅ አልቻለም። ስለዚህ እነ ታምራት ላይኔ ብቅ አሉ። እነ ታምራት፣ ፊት ፊት እየቀደሙ ጎንደሬዉን፣ ወሎዬዉን እየቀሰቀሱ ሕወሃት ያለ ምንም ችግር ወደ መሐል አገር እንዲገባ አደረጉ። ከዚያ አዲስ አበባ ሲገባ፣ ሚሊተሪዉን የያዙት ሕውሃቶች ስለነበሩ፣ እነ ታምራትን ወደጎን አድርገው፣ በቀላሉ ስልጣን ላይ ተቆናጠጡ። ይኸው እስከዛሬ ድረስ የነታምራት ቡድን የሕውሃት እንደራሴን አሽከር ሆኖ፣ እንወክለዋለን የሚሉት “አማራው” እንኳን ከኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል አገርህ አይደለም እየተባለ በኦህዴድ/ኢሕአዴግ ካድሬዎች በግፍ ሲፈናቀል፣ የጎንደር ለምለም ግዛት የነበረው ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ እንዲዞር ሲደረግ፣ ከጎንደር መሬት ተቆርሶ ለሱዳን ሲሰጥ ምንም ማድረግ ያልቻለ ቡድን ሆኗል።

አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው እየተፈፀመ ያለው። ሻእቢያ በአገር አቀፍ ድርጅቶች እመኔታ የለውም። ሥለዚህ የራሱን የሚያምንበትን ድርጅትን አጠናከረ። ደሚትን። ግንቦት ሰባትም ከደሚት ጋር እንዲሰራ ሻእቢያዎች ሲጠይቁ (ምናልባትም ሲያዙ) ግንቦት ሰባት ለመስራት ተሰማማ። ልክ እነ ታምራት ለህወሃት እንደሆኑት፣ ግንቦት ሰባት ደግሞ ለደምሚት ለመሆን ተዘጋጀ። ይኸው የሻእቢያ ልጅ የሆነውን ደሚት እየካቡልን ነው።

እስቲ አንድ ሴንሪዮ እንመልከት።እንበል ጦርነት ተከፍቶ፣ ግንቦት ሰባትና ደሚት አሸንፈው አዲስ አበባ ገቡ። ሚሊተሪዉን የያዘው ደሚት እንደመሆኑ፣ ዶር ብርሃኑ አዲሱ ታምራት ላይኔ ሆነው፣ የደሚቱ መሪ ደግሞ አዲሱ መለስ ዜናዊ እንደሚሆኑ መቼም መገመት አያቅተንም። ግንቦት ስባቶች እኛ ሥልጣን ለመያዝ አይደለም፣ ወያኔ ከወደቀ በኋላ አገር አቀፍ ኮንፈራንስ ይደርጋል ይላሉ። ነገር ግን ሕወሃት ያኔ እነ በየነ ጰጥሮስን፣ እነ ሌንጮን ሰብስቦ ኮንፍራንስ እንዳደረገው፣ በደሚትና በግንቦቶች የሚደረገው ኮንፈራንስ፣ የይስሙላ ነው የሚሆነው። ጠመንጃ ያለው ኃይል ነው የሚገዛው። እርሱም ደሚት። በመሆኑም የግንቦት ሰባት ዘመቻ፣ በርግጠኝነት ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን፣ ቀዳሚዉን ሕውሃት በዳግማዊ ሕውሃት በመተካት፣ በቅድመ ባድመ አመታት እንደነበረው፣ ኢትዮጵያ በእጅ አዙር በሻእቢያ እንድተገዛ የሚያደርግ ነው። አንድ በሉ።

ሌላው እነ ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር የመሳሰሉት ሲዳከሙ ደሚት ለምን ሊጠናከር እንደቻለ እንድንመረመር እፈልጋለሁ። እስቲ አስቡት፣ በትግራይ ሕውሃት ብዙ ግፍ ቢፈጸምም፣ በመሀል አገር በተለይም በኦሮሚያ እንደተፈጸመው አይሆንም። ታዲያ ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር ብዙ ወታደር ሳይኖራቸው፣ እንዴ ደሚት ብዙ ወታደሮች ሊኖረው ቻለ ? መልሱ ቀላል ነው። ሻእቢያ ጠንካራ ግንቦት ስባት፣ ጠንካራ የአርበኞች ግንባር እንዲኖር አይፈልግም። ሻእቢያ፣ ደሚት የበላይነቱን የያዘበት ኃይል እንዲኖር ነው የሚፈልገው።(ያኔ ሕወኃት የበላይ ሆኖ እንደነበረው) ሁለት በሉ።

በሶስተኛነት የማነሳው የግንቦት ስባት የፖለቲካው አመራር ምን ያህል በኤርትራ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያውቅል በሚለው ላይ ነው። ግንቦት ሰባት ለአራተኛ ጊዜ ወታደርች እንዳስመረቀ አንብበናል።(ከዚህ በፊት የተመረቁት የት እንዳሉ ባናውቅም) የግንቦት ስባት አመራሮች ምን ያህል እርግጠኛ ናቸው ስልጠና መደረጉን ? በድህረ ገጾች የምናየው ፣ በኢሳት የምንሰማው የለየለት የሻዕቢያ ድራማ ስላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አላቸው ? ልሳሳት እችላለሁ፣ በስፋራው ሄዶ መረጃ ሰብስቦ የመጣ ከፍተኛ የአመራር አባል አለ ብዬ አላስብም። ምናልባት ዶር ብርሃኑ ነጋ እራሳቸው ቢያንስ አለ የሚሉትን ጦር ለማበረታት፣ ለተመረቅት የምስክር ወረቀት ለመስጠት፣ ያለዉን ሁኔታ በአይናቸው አይተው ደጋፊዎች ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ በድፍረት ለመናገር ይረዳቸው ዘንድ ለምንስ ወደ ኤርትራ አይጓዙም ? ሌላው ኢትዮጵያዊ ወደ አስመራ ሄዶ እንዲዋጋ ጥሪ እያቀረብን፣ እኛ ግን አካባቢው ለመድረስ የምንፈራ ከሆነ እኛ የምንመራው ድርጅትስ እንዴት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል ? በሞራል አንፃርስ ትክክል ነው ወይ ?
በግሌ ለመብቱና ለነጻነቱ ፣ ለአገሩ ሲል ነፍጥ የሚያነሳ ሰው በጣም አከብራለሁ። ነገር ግን እርሱ ቤቱ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ፣ የድሃው ልጅ ሕይወቱን እንዲገብር የሚያዝ መሪ ግን አይመቸኝም። ለአቶ አንዳርጋቸው አክክብሮት ደካማ አመራር ነው። አራት በሉ።

ግንቦት ሰባቶች እንዲሁ ይፎክራሉ እንጂ ጦረኞች አይደሉም። አንደኛ ጦረኛ ሰው ብዙ አያወራም። የጦረኛ ሰው ቋንቋዉ የጥይት ድምጽ እንጂ ቴሌዝዥን እና ኢንተርኔት አይደለም። ዶር ብርሃኑ የአፍ ጀግና ግን የባሩድ ሽታ የሚፈሩ ናቸው። እንደኔ ካሉ በፌስ ቡክና በድህረ ገጽ ከሚለቀልቁ በምንም አይለዩም። ለዚህም ነው ዉጤት አላመጣችሁበትና፣ አያምርባችሁምና፣ ከሻእቢያ ጋር የምታደርጉትን ዳንኪራ አቁሙና፣ ጎበዝ በሆናችሁበት፣ በተካናችሁት፣ ዉጤት ልታመጡበት በምትቹሉት ሥራ ተጠመዱ የምላቸው። እስቲ አስቡት፣ አሁን ማራዶና ተከላካይ ቢሆን ? የነ ዶር ብርሃኑም ነገር እንደዚያ ነው።
እንግዲህ የሚሰሙ ከሆነ ምክሬን በድጋሚ እለግሳለሁ። ከሻእቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጥሰው፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችና ቡድኖች ጋር አብረው መስራት ቢጀመሩ ጥሩ ነው። ሻእቢያ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ መዉጣት አለበት። ሻእቢያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ ህዝብ፣ ለምስራቅ አፍሪካ በሙሉ መወገድ ያለበት ነቀርሳ ነው። በዉጭ ያለነው እኛ ኢትዮጵያዉያን እንዳንስማማ ያደረገን፣ በጉዳያችን ገብቶ የከፋፈለን ሻእቢያ ነው። ከሻእብያ ጋር በመስራታቸው ቅንጣት ያህል በወያኔ አገዛዝ ላይ ያስመዘገቡት ድል የለም። በአንጻሩ ወያኔን ሊያንበረክክ የሚችል የተቃዋሚዎች አንድነት እንዳይኖር ግን፣ ሻእቢያ አንዱና ትልቁ ምክንያት ሆኗል።
አውቃለሁ፤ ቁስል ያለበት ሰው ቁስሉ ሲነካ ያመዋል። ግንቦቶችም በጻፍኩት ነገር ሊናደዱ ይችላሉ። ነገር ግን የማታ ማታ እዉነቱን ስለነገርናቸው ያመሰግኑናል ብዬ አሰባለሁ።

%d bloggers like this: