የኢሕአዴግ ስልጠናዎችን የነፃነት ኃይሎች መተዋወቂያ፣ መደራጃ፣ መረጃ መለዋወጫ በማድረግ ስልጠናዎቹ የራሱን የኢሕአዴግ ጉድጓድ መማስ አለባቸው

በ ታደሰ ብሩ 

image

ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዩኒቨርስቲ ሥራዬ በሚተርፉኝ ሰዓቶች እዚሁ ከተማ – ለንደን – ይገኝ በነበረ Boston College in London በሚባል አስገራሚ የመንደር ኮሌጅ ውስጥ ማስተማር ጀምሬ ነበር። ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ የኮሌጁ ተማሪዎች ከበርማ (የአሳን ሱቺ አገር) የመጡ ናቸው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የምናገረውን አይሰሙም፤ እስኪደክመኝ አስረጅቼ ስጠይቃቸው ይደነጋገራሉ። ተማሪ ካልገባው “ስህተቱ የኔ ነው” ብዬ ስለማምን የተለያዩ ዘዴዎችን ፈጠርኩ። ለወትሮው የኔ ክፍሎች “ደባሪ” ከሚባሉት ወገን እንዳልሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ። እዚህ ኮሌጅ ውስጥ የነበረኝን ክፍል ማራኪ ማድረግ ግን ተሳነኝ። ከተማሪዎቹ ጋር ጥሩ አግባብ አለኝ፤ ትምህርቱ ግን እየተካሄደ አልነበረም። 

ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ምስጢሩን ደረስኩበት። አንደኛው ተማሪዬ ፀጉሩን እያሻሸ “ይህንን ኮርስ አውቀን ለመውደቅ እየተማርን ስለሆነ ብዙ አትልፋ” ሲል “መከረኝ” ። ውይይታችን የሚከተውን በሚመስል ሁኔታ ቀጠለ።

እኔ: ምን ማለት ነው ለመውደቅ አቅዶ መማር? 
እሱ: ይኸውልዎ፣ እኛ እዚህ አገር የመጣነው ለመማር ሳይሆን “ድህነትን ለማሸነፍ ነው”። የተማሪ ቪዛችን በሳምንት የተወሰኑ ሰዓታትን (ሁለት ቀናት ያለኝ ይመስለኛል) የመሥራት መብት ይሰጠናል። በእሱ የኮሌጁን ከፍለን ትንሽ አስተርፈን ራሳችንንም ቤተሰቦቻችንን መርዳት ነው ዓላማችን። 
እኔ: አዝናለሁ፤ ግን ይህ ለመውደቅ ከመማር ጋር ምን ያገኛኘዋል? እንዲያውም ደክማችሁ ያመጣችሁትን ገንዘብ የከፈላችሁበትን ትምህርት በትጋት እንድትከታተሉ ያደርጋችኋል። 
እሱ: በህግ በሚፈቀድልን ሰዓት የምንሠራውማ ከትምህርት ክፍያና ከቤት ኪራይ አያልፍም። አሁን ክፍል ውስጥ የምታየው ሰው ሁሉ ማታ ሲጠረግ፣ ሲያጥብ ያደረ ነው። 
እኔ: የምትነግረኝ ሁሉ ቢያሳዝንም “ለመውደቅ መማር” ያልከውን አይገልፀውም። 
እሱ: ይህንን ኮርስ ካለፍን እንመረቃለን። ከተመረቅን ቪዛችን ያልቃል። አሁን እኔ እያንዳንዱን ኮርስ እየደገምኩ የሁለት ዓመቱን ትምህርት 4 ዓመት አቆየሁት። አሁን ማለቁ። አንድ ሴሜስተር የመቆየት ተስፋ ያለኝ ይህንን ኮርስ ከወደቅሁ ነው። 

በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ ለተማሪዎቼ ግልጽ ድርድር አቀረብኩ። “የማርክ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሌላ ርዕስ ነው። ከፈለጋችሁ ትምህርቱን አውቃችሁትም እያለ በታቀደ ሁኔታ ፈተና መውደቅ ትችላላችሁ፤ ማወቃችን ፈተና ያሳልፈናል ብላችሁ አትፍሩ። ሆኖም የከፈላችሁበት ነውና ትምህርቱን ብትማሩት ለሕይወታችሁ ይጠቅማችኋል። በዚህ መንፈስ ለመማር የምትፈልጉ እነማን ናችሁ?” ጥቂት እጆች ወጡ። መማር የሚፈልጉትን ወደ ፊት መስመር በማምጣት ትኩረቴን እነሱ ላይ አደረግሁ። ሌሎች እንዳይረብሹን፤ ሌላ የሚጠቅማቸውን ነገር እንዲሠሩ ተስማማን። ከዚህ ቢያንስ ሁለት ጥቅሞችን አግኝተናል ብዬ አስባለሁ፤ 1ኛ) መማር የሚፈልጉትን በተሻለ ትኩረት መርዳት ቻልኩ 2ኛ) ሌሎችም ሰዓቱን ይበልጥ ለሚጠቅማቸው ነገር ተጠቀሙበት – የተወሰኑ ቡድኖች ክፍለ ጊዜውን የሞባይል አፕሊኬሽኖች አጠቃቀምንና ሞባይል ራሱን መፍታት መግጠምን ተማማሩበት፤ ጥቂት የማይባሉትም “ሳያስጠጡ ተኙበት”። ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ኮሌጁ ራሱ የጥራት ደረጃ ባለሟሟላቱ ተዘግቷል።

ይህንን ማስታወሻ እንድጽፍ ያደረገኝ የሰሞኑ የኢሕአዴግ የግዴታ ስልጠና ነው። ለመማር ያልተዘጋጀን ሰው በግዴታ ማስተማር ማደንዘዝ ነው። ኢሕአዴግ የግዴታ ስልጠና እየሰፋ በሄደ መጠን ራሱን ይበልጥ እያስጠላ፤ ሰልጣኙን ደግሞ በተወሰነ መጠን እያደነዘዘ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። ሰልጣኖች ብቻ ሳይሆኑ አሰልጣኖችም እያቅለሸለሻቸው እንደሚያሰለጥኑ እየሰማን ነው። ሕወሓት ኢሕአዴግን ደነዝ አደረገው። ኢሕአዴግ በተራው በግዴታ ስልጠና ሕዝብን ሊያደነዝዝ ተነስቷል። ይህንን የኢሕአዴግ ስልጠና ለሚረባ ነገር ማዋል ካልቻልን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። የኢሕአዴግ ስልጠናዎችን የነፃነት ኃይሎች መተዋወቂያ፣ መደራጃ፣ መረጃ መለዋወጫ ማድረግ ይገባል። የኢሕአዴግ ስልጠናዎች የራሱን የኢሕአዴግ ጉድጓድ መማስ አለባቸው። እንደ ኮሌጁ ሁሉ እነዚህ የግደታ ስልጠናዎች የኢሕአዴግን እድሜ ማሳጠር ይኖርባቸዋል።

%d bloggers like this: