የ‹አማራ›ና ‹ቅማንት› ጉዳይ

በ ሙሉቀን ተሰፋው

የ‹አማራ›ና ‹ቅማንት› ጉዳይ
=====================

ይህን ጉዳይ ስሸሸዉ የቆየሁት ነገር ነዉ፡፡ እርግጥ አንድ ጊዜ ፋክት መጽሄት ላይ ነካክቸዉ ነበር (ያኔ ኤዲት ሲደረግ የኔን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ይዞ ባይወጣም) ግን እስከ መቼ እየሸሸሁትስ እዘልቃለሁ? የማያስኬድ ነገር ሲሆንብኝ ይህን ሀሳብ ለመሞነጫጨር ተገደድኩ፡፡ ያለዉን ነበራዊ ሁኔታ በዚህ መልኩ ማስቀመጡ ጠቀሜታም ጉዳትም ይኖረዋል፡፡
ጉዳቱ አንዳንድ የአስተሳሰብ ስንኩላን ከእሳቱ ላይ ቤንዚን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ መልኩ ጠቀሜታዉ ደግሞ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በመጨመር እየተፈጠረ ላለዉ ሁናቴ መፍትሄ ሊያፈላልጉ የሚችሉ ግለሰቦችና ምሁራን አይጠፉም፡፡ ጥቅሙንም ጉዳቱንም በመመዘን ለአንባቢያን ማሳወቁ ይጠቅማል ብየ ስላሰብኩ በሚከተለዉ መልኩ አስቀምጨዋለሁ፡፡
የዛሬ ወር አካባቢ መሆኑ ነዉ፡፡ ከአዘዞ አጼ ቴዎድሮስ አዉሮፕላን ማረፊያ ወደ ፒያሳ አንዲት ቢጫ ታክሲ ኮንትራት ይዣለሁ፡፡ የታክሲዉ አሽከርካሪ ደስተኛ አለመሆኑ ፊቱ ቢመሰክርም ምን እንደሆነ መጠየቅ አልፈለግኩም፡፡ ግን በራሱ ጊዜ የሆነዉን ነገረኝ፡፡
እድሜዎ በአርባዎቹ መካከል የሚገኘዉ የታክሲ አሽከርካሪ ያስከፋዉ ነገር ሚስቱንና የልጆቹን እናት ያጣበት ምክንያት ነዉ፡፡ ‹‹አስራ ሰባት (17) አመታት ከሚስቴ ጋር አብረን ስንኖር ስለ እርሷ ዜግነት(?) የማዉቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ ሰዉነቷ ብቻ በቂዬ ነበር፡፡ እዉነቴን ነዉ የምልህ የጎንደር ልጅ ከመሆኗ ዉጭ የማዉቀው አልነበረኝም፡፡ በጋብቻችን ለአቻዎቻችን አርኣያ የምንሆን ነበርን፡፡ በትዳራችን 3 ልጆችን አፍርተናል፡፡ የመጀመሪያዋ 16 አመቷ ነዉ፡፡ ባለፈዉ የጥቅምት መድሀኒዓለም እናቷ ደወለችልኝና ለመድሀኒዓልም ዝክር ዝግጅት ታግዘኝ ላካት አለችኝ፡፡ እኔም በደስታ እናቷን እንድታግዝ መሄዷን በደስታ ተቀበልኩ፡፡ የጥቅምት መድሀኒዓለም አልፎ ግን ከነገ ዛሬ ትመጣለች እያልኩ ከልጆቼ ጋር ብናያት የዉሃ ሽታ ሆነች፡፡ ስልክ ስንደዉል ስልኳን ዘግታለች፡፡ መጨረሻ ቤተሰቦቿ ካሉበት ቦታ ትክል ድንጋይ ሰዉ ተላከ፡፡
‹‹ልጃችን ‹አማራ› አግብታ አትኖርም! የሚል መልስ ከእናቷ ሰሙ የተላኩት ሰዎች፡፡ ሶሰት አመት ያልሞላዉን ህጻን ልጅ እና ሌሎቹንም ልጆቿን ትታ ለመቅረት እንደወሰነች ሰማሁ፡፡ በቄስ በሽማግሌ አስጠየቅኳት፡፡ ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ! ልጆቼ ሲያድጉ ሰራተኛ አላያቸዉም፡፡ ሙሉ በሙሉ የሚያስፈልጋቸዉን ሁሉ እርሷ እና እኔ ነን የምናሟላቸዉ፡፡ ሰራተኛ አሁን አስገብቼ ለትምህርት ቤት ምሳ እንድትቋጥር ሳደርግ ልጆቹ ሳይበሉት እየተመለሱ እርሃብ ሊገድላቸዉ ሆነ፡፡ አሁን የቤቱንም የዉጩንም ስራ ብቻየን ይዠዋለሁ›› በማለት ልብን የሚሰብረዉን ግለ ታሪክ አጫወተኝ፡፡
ሌላዉ አጋጣሚ ደግሞ እንደዚህ ነዉ፡፡ በህዝብ ትራንስፖርት ወገራ አዉራጫ ዉስጥ ኮሶዬ ከሚባል ቦታ ደርሼ ለመምጣት ተሳፈርኩ፡፡ መኪና ውስጥ ከፖለቲካ ዉጭ የሚወራ ወሬ መጥፋቱን አስተዋልኩ፡፡ በቃ ግማሹ መንግስትን ተቃዉሞ ከፊሉ ደግሞ መነታረክ ነዉ፡፡ ስሄድ ምንም ሳልናገር ደረስኩ፡፡ ስመለስም ሌላ የፖለቲካ ንትርክ ካለባት ሚኒባስ ውስጥ ገባሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ- የፓርላማ ሰዎች ያን ያክል ውይይት አያደርጉም፡፡ ወደ ጎንደር ከተማ ስንቃረብ ግን ፖለቲካዉ ‹ቅማንት- አማራ› ሆነ፡፡ አንድ መሀል ሰፋሪ ወጣት ነገሩን አቀጣጠለዉ፡፡
ከአምባ ጊዎርጊስ የተሳፈረ ግለሰብ ሸምበቂት ከምትባል አነስተኛ መንደር ሲወርድ ‹አቀጣጣዩን› ልጅ ‹ቅማንት ስለሆንክ እወድሀለሁ!› ብሎት ወረደ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ይህ ጎጠኝነት ገበሬዉ ድረስ ስር መስደዱ አሳዘነኝም አንገበገበኝም፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ከጀርባየ ካለዉ ወንበር የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ሊደባደቡ ሲታገሉ ዞርኩ፡፡ መኪናው ቆሞ ሰዎቹን መገላገል ያዝን፡፡
ከአፍታ በፊት በወዳችነት ሲያወሩ የነበሩት ግለሰቦች ለምን እንደተጣሉ አጣራንና የበለጠ አዘንን፡፡ ሊደባደብ የሚገለገለዉ ሰዉዬ ‹እኔ በአባቴ ቅማንት ነኝ፡፡ እርሱም ቅማንት ነዉ፡፡ የሚኖረዉ ጎንደር ዙሪያ ሆኖ ሳለ እባክህ በእናንተ አካባቢ ‹ኮሶየ› ምሽት ፈልግልኝ አለኝ፡፡ ጎንደር ዙሩያ ጠፍቶ ነዉ ኮሶየ ድረስ ምሽት ፍለጋ የምትመጣዉ? ስለዉ ከዚህማ ሁሉም አማራ ሆነብኝ፡፡ ቅማንት ከእናንተ አካባቢ ብዙ አለ ብየ እኮ ነዉ ይለኛል፡፡ አማራ ቢሆኑ ምን ችግር አለዉ? ብየ ስመልስለት ‹ደሞ ከነዚህ ‹እንትኖች› ጋር ነዉ የምጋባዉ? ሲለኝ ስሜቴን መቆጣጠር አቃተኝ!›› በማለት ሲያብራራ እኔ የምናገረዉ ስላልነበረኝ ዝም አልኩ፡፡ አብረዉ የነበሩ ሊደባደቡም የከጀሉ፣ የተጨቃጨቁም፣ ብዙ ያወሩም አሉ፡፡
የተሳደበዉ ግለሰብ ዝምታን መርጧል፡፡ ጥፋተኛነቱን ያመነ ይመስል ነበር፡፡
ግን ከዚህ ሁሉ ምን እንመለከታለን? ዘረኝነትና ጎጠኝነት ገጠር ካልተማረው ማህበረሰብ ድረስ ገብቷል፡፡ በአርማጭሆ፣ ወገራና መተማ በዚህ አመት ብቻ በርካታ ጥንዶች ትዳራቸዉን አፍርሰዋል፡፡ ልጆቻቸዉን በትነዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን ያሉ ፍርድ ቤቶች በዚህ አመት ያስተናገዱት የፍች ጥያቄ ከዚህ በፊት ካለዉ ዘመን ጋር የሚነጻጸር አይደለም፡፡
ለእኔ እስከሚገባኝ ቅማንትና አማራ መካከል ምንም ልዩነት አላየሁም፡፡ የሚኖረበት ቦታ፣ የሚናገሩት ቋንቋ፣ የሚያመልኩት ሀይማኖት፣ የሚመገቡት…. ሁሉ ተመሳስሎ ሳለ ለምን ግን መለያየት አስፈለገ? የ‹ቅማንት ብሄረሰብ› አለባቸዉ በተባሉ ቦታዎች ሁሉ ዞሬ ለመታዘብ እንደቻልኩት ከ‹አማራዉ› የተለየ ቋንቋና ባህል አልገጠመኝም፡፡ ይህ መሬት ላይ ያለ እዉነታ ነዉ፡፡ ቅማንት የሚባል ቋንቋ ነበር፡፡ አሁንም በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች እንችላለን ያሉኝ አሉ፡፡ አባ ወንበሩ መርሻ (የቅማንት መሪ) ከመሞታዉ በፊት ይህን ጉዳይ አረጋግጠዉልኛል፡፡
በእኔ እምነት ይህ ቋንቋ ፈጽሞ ከመጥፋቱ በፊት ዩንቨርሲቲዎቻችን (በተለይም የጎንደር ዩንቨርሲቲ) መዝገበ ቃላትና ሰዋሰዉን ማስቀረት አለባቸዉ፡፡ ፈቃደኛ የሖኑ ሰዎችም ሊማሩበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መሰረታዊ እዉነታ መሬት ላይ ባለበት መልኩ እርስ በራስ ቅራኔ ውስጥ መግባቱ እጅግ አስቀያሚና ኋላ ቀር የሆነ አስተሳሰብ ነዉ፡

%d bloggers like this: