አማራ የሚባል ሕዝብ አለ የለም?

By Biruk Sisay

አማራ የሚባል ሕዝብ አለ የለም የሚለው ክርክር ሲነሳ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር በአብዛኛው “አማራ የለም” ብለው የሚከራከሩት ሰዎች ‹አማራ›ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የወጡ መሆናቸው እና በተቃራኒው ደግሞ “አማራ የሚባል ዘር አለ” ብለው በመሞገት ‹አማራ የለም› በሚሉት ሰዎች ላይም አብዝተው የሚንጨረጨሩት [የሚናደዱት] ሰዎች ከሞላ ጎደል ‹አማራ› ተብሎ ከተሰየመው ማንነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸው ነው፡፡ የ‹አማራ› ሕልውና ከተጠቃሹ ሕዝብ በላይ ከሕዝቡ ውጭ ለሆኑ የብሔረሰብ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን በማያወላውል ሁኔታ በጉልህ የሚታይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባትም ዓለም ሃብቱ እንደሚሉት ‹አማራነት› ከእሱ ውጭ በሆኑ ኃይሎች የሚገለጽ ማንነት ነው የሚለውን እይታ የሚያረጋግጥ አድርጎ መውሰድ የሚቻል ይመስላል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ተያያዥ ጉዳይ የራሳቸውን ብሔረሰባዊ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ እና ፕሮፖጋንዳ ‹አማራና የአማራ ገዥ መደብ› ብለው በፈረጁት እና ባስተዋወቁት ‹ጠላት› አንጻር ያቀጣጠሉትና ሲያራምዱ የነበሩት የአንዳንድ ብሔረሰብ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን የአማራ ማንነት አለመኖርን እንደ ትልቅ ኪሳራ አድርገው ስለሚቆጥሩት ይሄን ስያሜ መተው የሚዋጥላቸው ነገር አይመስልም፤ ምክንያቱም የ‹አማራ ማንነት› መኖር ስያሜው ከሚወክለው ሕዝብ በላይ እነሱ ለሚመሩት ብሔረሰባዊ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ መኖርም ወሳኝ ነውና፡፡

በወቅቱ [በ1983 ዓ.ል] በዚህ አይነት ከውጭ ወደ ውስጥ (ከላይ ወደ ታች) በሆነ የተዛባ ምልከታ እና የገዥዎችን ፍላጎት ባስቀደመ ተንኮል በተሞላበት አካሄድ ከአካባቢው በመቀጠል ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በኩራት በሚናገር ማህበረሰብ ላይ አዲስ የአማራነት ማንነት ከመጫን ይልቅ ሕዝቡ በኩራት የሚዝፍንለትን ጎጃሜነቱን፣ ሸዌነቱን፣ ወሎዬነቱን፣ ጎንደሬነቱን፣… ዕውቅና በመስጠት ማንነቴ የሚለውን ኢትዮጵያውይነቱን ማክበር በጣም ቀላል ነበር፡፡

የአማራነት ማንነት ምልከታ ህብረተሰቡ ውስጥ እንደመኖሬ መጠን እና ካለኝ ቅርበት አንፃር (ቢያንስ የኖርኩባቸውን የጎንደርን እና የወሎን ማህበረሰብ ስሜት አውቃለሁ) ከማህበረሰቡ ስነ ልቦና የተረዳሁትን እንዲሁም ከተለያዩ የታሪክ መፃሀፍት በማንበብ ከተገነዘብኩት አንፃር፤

• አማራ የሚወክለው ቦታና አካባቢን፣ ዘውግ(ነገድ)ን
ወይስ ሃይማኖትን ነው?
• የአማራነት ማንነት ጊዜ ያመጣው ወይስ ቀድሞ የነበረ?
• አማራ የሚለው ቃል ከታሪክ አንፃር ምን ይመስላል?

የሚሉትን ጥያቄዎች እንደሚከተለው አብራራለሁ

1ኛ) በመጀመሪያ አካባቢን የሚወክልበት ጊዜ ነበር

በታሪክ ድርሳናት እንደተቀመጠው አብዛኛዎቹ የመካከለኛው ዘመን አፄዎች (በተለይ ከኦሮሞዎች ወረራ እና መስፋፋት በፊት ባለው ዘመን የነበሩት ነገስታት) መነሻ እና ማዕከል የነበረው አካባቢ የአማራ አገር (ቤተ አማራ) ይባል ነበር። ይህ ቦታ በአሁኑ ጊዜ መንዝ፣ ጃማ፣ ወረኢሉ፣ ተንታ አጅባር፣ መካነ ሰላም፣ ወግዲ ከላላ፣ ማሻ ፊጦ፣ መቅደላ፣ ዳውንት፣ አማራ ሳይንት…ወዘተ የሚያጠቃልል ሲሆን በአሁኑ መንግስት አማራ ሳይንት የሚባል ወረዳ አማራ የሚለውን ቃል ወርሶ ይገኛል። በአጠቃላይ ምዕራብ ወሎ እና የተወሰኑ አዋሳኝ የሸዋ አካባቢዎችን ያካትት ነበር። ከኦሮሞዎች ወረራ በፊት አሁን ወሎ የሚባለው አካባቢ ቤተአማራ (የአማራ አገር)፣ አንጎት፣ ላስታ፣ ደዋሮ እና ፈጠጋር በከፊል (ዳውሮ አላልኩም) ወዘተ በሚባሉ የአካባቢ ግዛቶች ይታወቅ ነበር።

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ትልቋ ኢትዮጵያ፡ የብዙ ነገዶች ማህበረሰብ በሚለው መፅሀፋቸው ስለ አማራ ሀገር እንደሚከተለው ብለዋል፡

የትልቋ ኢትዮጵያን የፖለቲካና የባህል ማዕከል ለመመሥረት አሥፈላጊ የሆነውን ጥረት ለቀሰቀሱና ለአሥፈፀሙ አማራ በተሰኘ ክፍለሀገር ይኖሩ ለነበሩ ቡድኖች ምሥጋና ይገባቸዋል። የአማራ አገር የሚገኘው በአሁኑ በወሎ ጠቅላይ ግዛት [መፅሀፉ የተፃፈው በኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው] በስተደቡብ ሲሆን በታሪክ የታወቀው የአማራ ክፍለሀገር አዋሳኞች በምዕራብ በኩል የአባይ ወንዝና የአባይ መጋቢ የበሽሎ ጅረት፤ በሰሜን በኩል የአንጎትና የላስታ ክፍላተሀገራት፤ በምሥራቅ በኩል ወደ አፋር በረሃ የሚያሽቆለቁለው ሸንተረር እና በደቡብ በኩል የወንጭት ወንዝ ሲሆን ከደቡብ ወደ አማራ አገር የሚያደርሰው በተራሮች መሃል የሚያልፍ ከነ ሥሙ አህያ ፈጅ የተባለ ገደላ ገደል መንገድ ነው።

2ኛ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ይወክላል

አማራ የሚለው ቃል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከቦታ ወይም ከዘውግ/ነገድ/ ይልቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኝ የሆነን ህዝብ ሁሉ የሚወክል ነበረ፡ ይህም የሆነበት እኔ እንደሚመስለኝ ከዚህ አማራ ይባል ከነበረው አገር የተነሱ የመካከለኛው ዘመን አፄዎች (በተለይ በእነ አፄ አምደ ጽዮን እና አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን) የኦርቶዶክስ ክርስትያን ተከታይ ስለነበሩ እና ሃይማኖቱንም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያና እንዲሁም አሁን ኦሮሚያ ወደሚባለው ክልል አካባቢዎች ስለ አስፋፉ የእነሱ መነሻ የነበረው አካባቢ ማለትም የአማራ አገር (ቤተ አማራ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ስም ወክሎ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲያገለግል እንደ ነበር መገመት አይከብድም (አሁንም በዚህ ዘመን አማራ የሚለውን ቃል እንደ ሃይማኖት አድርገው የሚቆጥሩ ብዙ ናቸው)። አሁንም አማራ ነህ ወይስ እስላም? ተብሎ ይጠየቃል ። ይህ ማለት አንድ ትግራውይ፣ የአርሲ ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ ወዘተ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይ ከሆነ አማራ ነው ማለት ነው። እኔ ጎንደር ላይ ካጋጠመኝ ነገር የማስታውሰው፡ መስሪያ ቤቴ ያለችን አንዲት ወጣት ልጅ ሌሎች ሰዎች ቅማንት ናት ሲሉ ሰምቼ ስለነገሩ የበለጠ ለማወቅ አንድ ቀን “ቅማንት ነሽ ወይ?” ብዬ ስጠይቃት “ኧረ እኔ ተጠምቂያለሁ! አማራ ነኝ!” አለችኝ እንግዲህ ከልጅቷ መልስ አንፃር አማራ ማለት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ማለት እንጂ ነገድ ወይም ጎሳና ዘር እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ሙስሊም ወሎዬን “አማራ ነህ ወይ?” ብለህ ብትጠይቀው “ኧረ አይደለሁም! እስላም ነኝ” ብሎ ነው የሚመልሰው። በደቡብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ አካባቢ አሁንም ድረስ ኦርቶዶክስ ነህ እስላም ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ አማራ ነህ ወይስ እስላም ነው የሚባለው።

3ኛ) አሁን በተግባር ላይ ኢህአዴግ ለከፋፍለህ ግዛ አላማው ተግባራዊ ያደረገው ወሎን፣ ጎንደርን፣ ጎጃምን እና ሸዋን በመሸንሸን ቆራርጦ የፈጠረውና አሁን አማራ ክልል የሚባለውን ቦታ ይወክላል

አሁን አማራ ብሄር የሚባለውና የአማራ ክልል ተብሎ የተፈጠረው ቅርፅ በመጀመሪያ የተገኘው ከ70 ዓመት በፊት በጣልያን ወረራ ወቅት በቅኝ ገዥዎች ደልዳይነት ተፈጥሮ የነበረውን የአካባቢ ሽንሸና ፈርጅ በመዋስ ሲሆን ይህ የአሸናሸን ሁኔታ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት በማጥፋት የቅኝ አገዛዝ ዕቅድን ገቢር ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ በቀላሉ ስለታወቅ በወቅቱ በነበረው ትውልድ ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል። በወቅቱ ጣልያን የተጠቀመው አከላለል ከኢትዮጵያዊነት መለያ ጋር በማወዛገቡ የዚያኔው ትውልድ አዲሱን የአማራነት መለያ ከመቀበል ይልቅ እርሱን መካድ እና መቃወም መርጦ ኗሯል። በሚገርም ሁኔታ የፀረ ቅኝ ግዛት አርበኝነቱ ትግል ይገለፅ ከነበረባቸው መንገዶች መሀል አንዱ ይህንን ግዛታዊ ሽንሸና መካድ እና አለመቀበል ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች አንዲቷንም የጣልያን ክልል አደረጃጀት ሳያከብሩ፣ የጠላት ጦር ሰፍሮ በተገኘበት ስፍራ ሁሉ ትግላቸውን አድርገዋል።

ስለሆነም አማራ ተብሎ ለተፈረጀው ህዝብ የግዛቱ ክልል ምስረታ እና ተጓዳኝ የሆነ የማንነት ገፅታ ማላበስ የተቻለበት ሁኔታ የተከሰተው አሁን በኢህአዴግ ስርዐት ነው። የኢህአዴግ ኤክስፐርቶች ለአማራነት ከሚሰጡት ትርጉም ውስጥ ተበጥሮ ተበጥሮ የሚገኘው ጭብጥ አንድ ብቻ ነው። እርሱም አማራነት ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የቋንቋ መታወቂያወችን እንደመለያ አድርገው ለመቀበል የፈቀዱ አካላት በሙሉ፤ የራሳችን ነው ብለው የሚያስቡትን እንዲሁም የሚፈልጉትን ህዝብ እና ቦታ ከወሰዱ በኋላ የሚተርፈው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚታጎርበት ወይም የሚመደብበት ቦታ እና ማንነት ይሆናል። በመሆኑም ይህ ፈርጅ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ተቆርቋሪ የሆነውን እና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ተቀዳሚ መታወቂያው አድርጎ ሊወስድ የሚነሳውን ህዝብ በሙሉ የሚያካትት ነው።” ኦነግ እና ህወሀት እንዲሁም ሳይገባቸውም ሆነ እየገባቸው የእነሱን ተንኮል እና መሰሪ ሀሳብ የሚያራምዱ ሁሉ የ”አማራ ልሂቃን” ብለው የሚፈርጁት ደግሞ ከዚህ ፈርጅ የሚወጣውን የተማረ እና ለአገር ተቆርቋሪ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ነው።

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ከላይ በጠቀስኩት መፅሀፋቸው አማራ እና ኦሮሞ የሚባል ክልል እና ማንነት እንዳልነበረ እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፦

ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች በተለምዶ ራሳቸውን የሚጠሩት ቦረና፣ ጉጂ፣ አሩሲ፣ ሜጫ ወዘተረፈ ብለው ነው እንጂ ኦሮሞ ብለው አይደለም። አማርኛ ተናጋሪዎች በአገራቸው የመላው አማራ ማህበረሰብ ነን ብለው አባልነታቸውን ከቶ አጥብቀው አያውቁም። ማንነታቸውን ለመግለፅ በክፍለሀገር ደረጃ ወሎዎች፣ ጎጃሞች፣ ጎንደሮች፣ ሸዋወች አለበለዚያ ከዚያ ሁሉ የበላይ ከሆነው ስም አበሾች ነን ይላሉ። በአማርኛም ሆነ በትግረኛ አበሻ የሚለው ስም ተወላጅነቱ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሁሉ ጠቅላላ ስም ነው። የንጉሰ ነገስታቱ አቋም ራሱ ከክፍለ ሀገር በላይ የሆኑ የብዙሀን ነገድ ማህበረሰብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት ዜጎች ማህበረሰብ መሆኑ ለሁልጊዜ አንድነቱን አስታዋሽ ነበር። የነገስታቱም የህይወት ታሪክ ፀሀፊ “የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት” እያለ አዘውትሮ በማወደሥ ያነሳል……።

©ብሩክ ሲሳይ

%d bloggers like this: