ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ወዳጆች አፈራ? ጠላቶችስ ለምን ተነሡበት?

Eotcmk.org

“ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ…በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል ትን.ዕንባ.3፡17-19”

image

በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመደገፍና ለማጠናከር የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ ፈተናዎችን እያሳለፈ 22 ዓመታት ተጉዟል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዓመታት ጉዞው ባከናወናቸው መልካም ተግባራት ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ ወዳጆችን እንዳፈራ ሁሉ ጥቂት በተቃራኒው የቆሙ ስሙን በየጊዜው በክፉ የሚያነሱ ቡድኖችም ተነሥተውበታል፡፡

ወዳጆቹ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች ናቸውና በአገልግሎቱ ተማርከው በሚሠራቸው መልካም ሥራዎች ተስበው ቤተ ክርስቲያን ያለባትን የአገልግሎት ክፍተት ለመሙላት በጋራ ከማኅበሩ ጋር በመሥራት ሲተባበሩ፤ በአንጻሩ ጠላቶቹ ደግሞ የተለያዩ አጋጣሚዎችን እያስታከኩ ማኅበሩን ለመወንጀል እየተጣጣሩ ይገኛሉ፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ወዳጆች አፈራ? ጠላቶችስ ለምን ተነሡበት?

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ፈቅዶ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ወጣቶችን በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታቸው ጎን ለጎን በየአካባቢው ወደሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሔደው መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ፤ በተጨማሪም ወጣቱ ሀገሩንና ሕዝቦቿን አክባሪ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን በማስቻሉ ብዙ ወዳጆችን አግኝቷል፡፡

 

ከዚህም ሌላ የመናፍቃኑንና ቤተ ክርስቲያኒቱን እናድሳለን ብለው የተነሡትን የመናፍቃኑ ተላላኪ ቡድኖችን ሴራና የአክራሪ እስልምናውን እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፎ በማጋለጡ፣ ከክፉ ትምህርታቸው መመለስ ያልፈለጉ የተሐድሶ ቡድን አባላት ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ስለተወሰነባቸው እና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች እየተከታተለ ለዕድገቷና ለብልጽግናዋ በመሥራቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆችን አፍርቷል፡፡

 

ከዚህ በተቃራኒው የተሰለፉት ወገኖች ደግሞ ወጣቱን እንደጠፍ ከብት ወደ ማያውቀው የመናፍቃን አዳራሽ የመንዳት ልምዳቸው በመቋረጡና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመግባት የሚያደርጉት ሥርዓቷን የማፋለስ እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም አገልጋዮቿንና ምእመናኖቿን የማስኮብለሉ አካሔድ ማኅበሩ በክትትል በተለያዩ መረጃዎች ስለገለጠባቸው ማኅበረ ቅዱሳንን በጠላትነት በማየት ማኅበሩ እንዲፈርስ የማይቧጥጡት ዳገት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

 

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብለው የነበሩ ቢሆንም አሁን ባገኙት አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጀራዋን እየበሉ የሚኖሩ ወዳጆቻቸውን በማጠናከርና በማስፋፋት በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ከወዳጆቻቸው ተመድቦላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማዛባትና በጎቿን ለመበታተን ሌት ከቀን እየሠሩ ነው፡፡

 

ይኼ ዕቅዳቸው የሚሳካው እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዓት መጠበቅ የሚቆረቆሩ ማኅበራትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አጀንዳ በማድረግና እንዲበተኑ ክፉ ሥራ በመሥራት ነው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ይሔንን ከንቱ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግም በቤተ ክርቲያኒቱ የተለያየ ሓላፊነት ላይ የሚገኙትን የዓላማቸው አስፈጻሚዎች ሁሉ እየተጠቀሙ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡

 

ከዚህም ሌላ ድብቅ ዓላማቸው እንዲሳካ ተላላኪዎቻቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚሆን ነገር ግን ስውር ዓላማ ያለው ማኅበር እንዲመሠርቱና ከዚህ በፊት ከንቱ ተግባራቸው ታውቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታግደው የነበሩ ማኅበራት ሁሉ ከሞቱበት እንዲቀሰቀሱ እየሠሩም እያደረጉም ይገኛሉ፡፡

 

በቤተ ክርስቲያን ስም ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያቋቋሟቸውና የሚያቋቁሟቸው፣ ማኅበራትንም ሕጋዊ ዕውቅና ለማሰጠት እንዲያመቻቸው ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከኔ ሌላ ሌሎች አያስፈልጉም የሚል አቋም ያለው ማኅበር እንደሆነ ያስወራሉ፡፡

 

በእርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ደንብ ተከትለው በሚቋቋሙት ማኅበራት ላይ የማኅበሩ ጠላቶች ከሚያወሩትና ከሚያስወሩት አሉባልታ የተለየ አቋም አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን የሁለት ሺሕ ዓመታት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ትሁን እንጂ መንበሯ ከሊቀ ጵጵስና ደረጃ ወደ ፕትርክና ለማሳደግ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ መራራ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በዚህ ማለፏ ደግሞ ሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበት ዘመናዊ የአደረጃጀት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልቻለችም፡፡ ልጆቿንም ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ ለመምራት ሳትችል ስለቆየች እነዚህን ክፍተቶች የሚሞሉ አንድ አይደለም በርካታ ማኅበራት እንደሚያስፈልጓት ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ነገር ግን እኩያኑ እንደሚሉት ሳይሆን እነዚህ ማኅበራት ሲቋቋሙ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዕድገትና የአገልግሎት ሥምረት የሚንቀሳቀሱ ተልእኮአቸውና ዓላማቸው ተለይቶ የሚታወቅ፣ መንፈሳዊ ተግባርን ብቻ የሚፈጽሙ፣ የሚናበቡና በስልት ለአንድ ውጤት የሚተጉ ሊሆኑ ይገባቸዋል የሚል ጽኑ አቋም አለው፡፡

 

ይሔንን አቋሙን ደግሞ በርካቶች የሚደግፉት እንደሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የመናፍቃኑ ተላላኪዎች በቤተ ክርስቲያን ስም ያቋቋሟቸው ማኅበራት ከዚህ በፊት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥለውት የሔዱት ጠባሳ የሚታወቅ ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራት ላይ ግልጽ አቋም አለው፡፡ ከዚህም ሌላ እነዚህ የውስጥ ዐርበኞች ይኽ ስውር ዓላማቸው ያልታወቀባቸው ይመስል ማኅበሩን ለመወንጀል የማይለጥፉለት ታፔላ፣ የማይለፍፉት ወሬ የለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላቶች ስለማኅበሩ የሚያወሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ እና ሁሉም የሚገነዘበው ግልጽ እውነታ መሆኑን ባለማወቃቸው እናዝናለን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን ምንም ስውር ዓላማ የለውም፤ ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዳና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብና መመሪያን ሳያዛንፍ እየሠራ ያለ፤ በተሰጠውም መተዳደሪያ ደንብና ሓላፊነት መሠረት ከአባላቱ የሰበሰበውን የገንዘብ መዋጮ ገቢና ወጪ እያሰላ በውስጥ ኦዲተሮችም እያስመረመረ በመሥራት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ማኅበር እንጂ በወሬ የሚኖር አይደለም፡፡ ይሔንን አሠራሩንም ቀርቦ ማየት ይቻላል፡፡ አባላቱም በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው በጉልበታቸውና በመላ ሕይወታቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ እንጂ እንደ መናፍቃኑ ተላላኪዎች ለሆዳቸው ያደሩ፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነባቸው እዚህም እዚያም ደሞዝ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡

 

ማንኛውም አካል እንዲያውቅልን የምንፈልገው ሐቅ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰጠው ሓላፊነትና አባላቱም ለገቡለት ቃል ኪዳን ሃይማኖታቸው የሚፈቅደውን መስዋዕትነት ለቤተ ክርስቲያን ልዕልናና ክብር ለመክፈል የተዘጋጁ እንጂ በተዛባ አመለካከት ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉ አለመሆናቸውን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱ የሚታይ አሠራሩም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም የመናፍቃኑ ተላላኪዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላ ከአገልግሎታችን አንዲት ጋት ወደ ኋላ እንደማይመልሰን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡ ርእይና ተልእኮአችንን ለማሳካት ዛሬም ነገም እንሠራለን፤ ትናንትን ያሻገረን እግዚአብሔር ዛሬንም ያሳልፈናልና፡፡

ይህ ጽሑፍ ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም ወጥቶ የነበረና ታርሞ በድጋሚ የቀረበ ነው፡፡

 

%d bloggers like this: