መኢአድ-ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ካልተካሄደ የከፋ ሁኔታ ሊከተል ይችላል!!

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ካልተካሄደ የከፋ ሁኔታ ሊከተል ይችላል!!
image

በአንድ ሀገር የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ዘላቂ ሰላም መልካም አስተዳደርና የልማት ተነሳሽነት ሊኖር የሚችለው የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ የህዝቡ የስልጣን ባቤትነት የሚረጋገጠውም ወቅቱን ጠብቆ በሚካሄድ ሁሉን አቀፍ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅሜን ያሰጠብቁኛል፣በትክክል ያገለግሉኛል ይበጁኛል ብሎ ያመነባቸውን ተወካዮቹን በነጻነት በመምረጥ ዕውነተኛ የስልጣን ምንጭና ባቤትነቱን ለማረጋገጥ አልታደለም፡፡የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት ለጋሽመንግስታትንና በአጠቃላይም ዓለምአቀፊን ማህበረሰብ ለማታለል እንደሚሞክረው አንድም ጊዜ ቢሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ አልተረጠም፡፡

በእርግጥም በኢትዮጵያ ምድር ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቢካሄድ ኖሮ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ያሰገነጠለ የባህር በራችንን አሳልፎ የሰጠ ህዝብን በዘርና በቋንቋ የከፋፈለ፣ታርካችንንና የጋራ እሴቶቻችንን ያረከሰ በዘረኛ ፖሊሲው ትውልድን እያደነቆረ ብሔራዊ ስሜትን እየገደለ ያለን ቡድን ሊመርጡ የሚችሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለሀገሩ ቀናኢና ተቋርቋሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ኢትዮጵያዊ ስሜት፣ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ራዕይ እንዴለላቸው ከመጀመሪያ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለሆነም ወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት የፀጥታና የአፈና መዋቅሮቹን በማጠናከር ላለፉት 23 ዓመታት ኢትዮጵያን በኃይል ሲገዛ ቆይቷል፡፡

ወያኔ/ኢህአዴግ በአንድ በኩል የህዝብን የመደራጀት መብት በማፈን በሌላ በኩል “ጠንካራ ተቃዋሚ የለም”” እያለ ሲያፌዝ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ ተቃዋሚዎች ህዝቡን በዙሪያቸው በማሳለፍ የሚያስችል አማራጭ አጀንዳ እንደሌላቸው ሲነገር ነበር፡፡ የወያኔ መሪዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ 85% የሚሆነው አርሶ አደር ህዝብ እንደሚደግፋቸው ያለምንም ይሁንታና ሀፍረት በመኩራራት ሲናገሩ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያለው ሁኔታ እንደተለመደው ለመዋሸት የሚያመች አይደለም፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ህዝብን አደራጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን በተለይ አርሶ አደሩ ህዝብ በወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ላይ ያለውን የመረረ ተቃውሞ በተግባር አረጋግጧል፡፡ የመሬት ባለቤትነት መብቱን ተገፍፎ የወያኔ/ኢሕአዴግ ጭሰኛ በመሆኑ በድህነት እንዲማቀቅ የተፈረደበት የገጠሩ ወገናችን “ወያኔ ለፍርድ እንጅ ለምርጫ መቅረብ የለበትም” እያለ ነው፡፡ መኢአድ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲደረግ የበኩሉን ታሪካዊ ኃላፊነት እየተወጣ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በየአካባቢው የተቀጣጠለውን የታቃውሞ እንቅስቃሴ በኃይል ለማፈን በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በኩል የተቀናጀ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ሁኔታው ደርግ በውድቀቱ ዋዜማ ማንኛውም ታጣቂ ነጻ እርምጃ እንዲወስድ በግልጽ ካወጀው ጋር ተመሳሳይ አለው፡፡ በተለይ የመኢአድ አባላትና ደጋፊዎች በግልጽ ተኩስ ይከፈትባቸዋል፡፡ በየምክንያቱ ይከሰሳሉ ተይዘው ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ ከአቅም በላይ የሆነ የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ መሬታቸውን ይነጠቃሉ ንብረታቸውን ይዘረፋሉ፣ የቤታቸው የጣሪያ ቆርቆሮ ተገፍፎ ይወሰዳል ከዕድርና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲገለሉ ይደረጋሉ ቤተ-ክርስቲያን ገብተው እንዳያስቀድሱ ይከለከላሉ በምግብ ለስራ ለፍተው የሚያገኙት የእርዳታ እህል ይከለከላሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር በሰላም በተገኙበት በውድቀት ሌሊት ተኩስ ይከፈትባቸዋል፡፡ ቤታቸው ይቃጠላል፡፡ ንብረቶቻቸውና የቤት እንስሳቶቻቸውም አብረው ይቃጠላሉ፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ አካላትም ሕግና ስርዓትን እንዲሁም ስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማስከበር ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ለገዢው ፓርት የአፈና አገዛዝ ዋነኛ መሳሪያ እየሆኑ ነው፡፡ የተለያዩ ግፍና በደል የሚፈጸምባቸው አባሎቻችን የመክሰስ ዋስ የማቅረብ ለሌሎች ዋስ የመሆን መብቶታቸውን በፍትህ አካላላቱ እየተነፈጉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የመኢአድ አባላት በቅጥር ነፍ-ገዳዮች እንዲደበደቡ እንዲገደሉ ቤታቸው እንዲቃጠል ንብረታቸው እንዲዘረፍ ሚስቶቻቸው ሴት ልጆቻቸው እንዲደፈሩ እየተደረገ ነው፡፡
በአጠቃላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና እጅግ ዘግናኝ ትዕግስት አስጨራሽና ሕዝቡን ለአመጽ የሚያነሳሳ በመሆኑ መፍትሄ ካልተፈለገለት ከማንም ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡ መንግስት ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁኔታው በጠመንጃ ኃይል ለመቆጠጣር የሚያስብ ከሆነ ግን ለሚፈጠረው እሰከፊው ሁኔታ ተጠያቂው ራሱ የወያኔ/ኢሕአደግ መንግስት ነው፡፡
ማንም ወገን ሊገነዘበው የሚገባው አንገቢጋቢ ጉዳይ ቢኖር ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚትገኝ መሆኑ ነው፡፡ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደሚነገረን ሳይሆን በሀገራችን ድህነት ስራ አጥነት ረሃብና በሽታ ተንሰራፍቷል፡፡ በዚህ ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ውስብስብ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡
በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ብሔረሰቦች መካከል ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ህይወት ጠፍቶል፡፡ ህዝብ ተስድዶል፡፡ በአጠቀላይ በየአካባቢው ሰላም ደፍርሶ ህዝብ በፍርሃትና በጥርጣሬ የሚታይበት ሁኔታ ተፈጥሮዋል፡፡ መልካም አስተዳደርና ፍትህን ማስፈን ያለበት መንግስት በየአካባቢው ሽብርና ፍርሃትን እያነገሰ ነው፡፡

ከዚህ አስፈሪ ቀውስና ውጥረት ለመውጣት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ/ በመጭው ዓመት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ ሰላማዊና ዴሞክራሲየዊ ሽግግር ይደረግ ዘንድ
1. ለተቃዋሚ ፓርቲ አባሎችና ደጋፊዎቻቸው የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ
2. የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል
3. የምርጫ ቦርድ እንደገና እንዲዋቀር
4. በምርጫው ሂደት ውስጥ ነጻና ገለልተኛ ታዛቢዎችና ተቆጣሪዎች እንዲኖሩ
5. ለተቃዋሚዎች ለምርጫ የሚመደብ በጀት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ
6. ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዕኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለት ከዚህ በፊት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ መልስ እንዲያገኙና በአካባቢው የህዝብን ተቃውሞና ጥያቄ ለማፈን በተለይ ደግሞ በመኢአድ አባሎችና ደጋፊዎች እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰቆቃ እንዲቆም አበክረን እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግስት የያዘውን አደገኛ አካሄድና ግትር አቋም በማስቀየር ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ በአገራችን የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ለሚከተሉት ወገኖች ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣
በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ሊሰፍን የሚችለው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሲካሄድና የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ግን ከህዝብ ይሁንታና መልካም ፈቃድ ውጭ በጠምንጃ ኃይል አስገድዶ ዘላለም ሊገዛን ይፈልጋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላለመልቀቅ በሚፈጥረው ውጥረት ሀገራችን አሁን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ወደ ባሰ ቀውስ እንዳትገባ በተቀናጀ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ትግል ወያኔ/ኢሕአዴግ የያዘውን ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ለማስቀየር መላው ህዝባችን ከመኢአድ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
ለወያኔ/ኢሕአዴግ አባላት፣

የደርግን አገዛዝ ለመገርሰስ በተካሄደው የትጥቅ ትግል ምን ያህል ህይወት እንጠፋና ምን ያህል የሀገር ንብረት እንደወደመ ሁላችን የምናውቀው ነው፡፡ ሆኖም ግን ያን ያህል ህይወት የተገበረበት እና የሀገር ሀብት የወደመበት እህል አስጨራሽ ትግል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስገኘውን ፋይዳ አብረን እያየን ነው፡፡ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ሀገራችንን በማስገንጠል እና የባህር በራችንን አሳልፎ በመስጠት እንዲሁም ህዝባችንን በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል የደገሱልንን ጥፋት ዛሬም ሁላችንም እየተቋደስነው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን እነ አቶ ኃ/ማርያም እየተወዛወዙ ወደ ባሰ ጥፋትና ቀውስ እየመሩን ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ የገዢው ፓርቲ አባል በጊዜያዊ ጥቅም እና የስልጣን ፍርፋሪ ሳይደለል ስለታገሉበት ዓላማ እና አገሩ ስላለችበት ሁኔታ ቆም ብሎ ማሰብና የመሪዎቹን የጥፋት እርምጃ በመግታት ኢትዮጵያዊነቱን ማስመስከር ይጠበቅበታል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት

በአሁኑ ሰዓት በመንግስት ስም እየተወሰደ ያለው አቋም ሀገራችንን ወደ ከፋ ምስቅልቅልና የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚወስድ ነው በመሆኑም የመንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነውና ጥያቄያችንን በቀጥታ የቀረበለት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ በጥልቀት በመምከርና ገምቢ አቋም በመውሰድ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እናሳስባለን፡፡
ለመከላከያ ሰራዊት አባላት

ወያኔ/ኢሕአዴግ ህዝባዊ መሰረቱን አጥቶ ህልውናው በታጠቀው ክፍል ድጋፍ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች የህዝብን ስብዓዊና ዴሞክራሲየዊ መብቶች ለመርገጥና የአፈና አገዛዛቸውን ለመቀጠል የሚተማመኑት በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን የመከላከያ ሰራዊትም መሰረታዊ ተልዕኮ የሀገርን አንድነት፣ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ መሆኑን ተገንዝቦ የገዥው ፓርቲ መሳሪያ ባለመሆን ህገ-መንግስታዊና ታርካዊ ኃላፊነቱን መወጣትና የህዝብ ወገናዊነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር

28/12/2006 ዓ/ም

%d bloggers like this: